በአማራ ክልል ለሚከበሩ ኃይማኖታዊና ባህላዊ በዓላት…
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 6፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአማራ ክልል በቅርቡ የሚከበሩ ኃይማኖታዊና ባህላዊ በዓላት በድምቀት እንዲጠናቀቁ አስፈላጊው ዝግጅት እየተደረገ ነው አለ የክልሉ ባህል ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ፡፡
የቢሮው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አበበ እምቢያለ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷ በክልሉ በታሕሣሥ ወር መጨረሻ እና ጥር ወር ላይ የተለያዩ ኃይማኖታዊና ሕዝባዊ በዓላት ይከበራሉ፡፡
በዚህ መሰረትም ከታሕሣሥ 26 እስከ 29 ቀን 2018 ዓ.ም የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በላሊበላ እና ጥር 6 ቀን የዳግማዊ ቴዎድሮስ የልደት በዓል በጎንደር ከተማ በድምቀት ይከበራሉ፡፡
እንዲሁም ጥር 10 እና 11 ቀን የከተራና ጥምቀት በዓል በጎንደር፣ ላሊበላ፣ ምንጃር ሸንኮራ፣ ባሕር ዳርና በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ሃይማኖታዊና ባህላዊ እሴቱን በጠበቀ መልኩ የሚከበሩ ይሆናል፡፡
በተጨማሪም ጥር 13 የግዮን በዓል በሰከላ፣ ከጥር 14 እስከ 18 ቀን ድረስ ‘ጥርን’ በባሕር ዳር፣ ጥር 23 የአገው ፈረሰኞች ማህበር በዓል በእንጅባራ እንዲሁም ጥር 25 የመርቆርዮስ በዓል በደብረ ታቦር እና ሌሎች በዓላት ይከበራሉ፡፡
በዓላቱ ኃይማኖታዊና ባህላዊ እሴታቸውን ጠብቀው በድምቀት እንዲከበሩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ለዚህም በዓላቱ በሚከበሩባቸው አካባቢዎች በየደረጃው ኮሚቴዎች ተዋቅረው የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡
የቢሮው አመራሮችና ባለሙያዎች አስፈላጊውን ክትትልና ድጋፍ እያደረጉ ነው ያሉት ኃላፊው÷ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እንግዶችን ለማስተናገድ ዝግጅት እንደጀመሩ አመልክተዋል፡፡
ሆቴሎች፣ ሪዞርቶችና ሌሎች ተቋማት ለውጭና ሀገር ውስጥ እንግዶች የዋጋ ጭማሪ ሳያደርጉ ከዚህ በፊት በነበረው ዋጋ እንዲያስተናግዱ መግባባት ላይ መደረሱን ተናግረዋል፡፡
ለሆቴል ባለሙያዎችና አስጎብኚ ድርጅቶች እንግዶችን በምን መልኩ ማስተናገድና ማስጎብኘት እንዳለባቸው ሥልጠና መሰጠቱን ነው አቶ አበበ ያስረዱት፡፡
በክልሉ የሚገኙ ከ400 በላይ አስጎብኚ ድርጅቶች ቢሮው ባወጣው የዋጋ ተመን መሰረት ለውጭና ሀገር ውስጥ ቱሪስቶች አገልግሎት እንዲሰጡ አቅጣጫ መቀመጡን አብራርተዋል፡፡
የበዓሉ ታዳሚ እንግዶች በሁሉም አካባቢዎች የመኝታ፣ ውሃ፣ ስልክ እና ኤሌክትሪክን ጨምሮ ሌሎች መሰረታዊ አገልግሎቶችን እንዲያገኙ በቁርጠኝነት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
ወደ ላሊበላ እና ጎንደር ለሚጓዙ እንግዶች የትራንስፖርት እጥረት እንዳይከሰት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ተጨማሪ በራዎችን እንዲያዘጋጅ ውይይት መደረጉን አመልክተዋል፡፡
ስለሆነም በመላው ኢትዮጵያ እና ውጭ ሀገራት የሚገኙ ጎብኚዎች በክልሉ በሚከበሩ በዓላት በመሳተፍና የቱሪስት መዳረሻዎችን በመጎብኘት አይረሴ ጊዜን እንዲያሳልፉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ