በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በ18 ከተሞች የኮሪደር ልማት ሥራ እየተከናወነ ነው
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 6፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አሁን ላይ በ18 ከተሞች የኮሪደር ልማት ሥራ እየተከናወነ ነው አለ የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ፡፡
የቢሮው ኃላፊ ኃይለማርያም ተስፋዬ እንዳሉት÷ በክልሉ በተለይም በግብርና፣ ኢንቨስትመንት፣ ኢንዱስትሪ፣ ማዕድንና ሌሎች ዘርፎች በርካታ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው፡፡
ክልሉ እምቅ የመልማት አቅም ያለው መሆኑን ጠቁመው÷ በተደመረ አቅም በማልማት ምርታማነትን በማሳደግ ከተረጅነት የመውጣት ጥረት ተጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል፡፡
በክልሉ ከ70 በመቶ በላይ ሕዝብ በተለያዩ የግብርና ልማት ሥራዎች ላይ ተሰማርቶ እንደሚገኝ የገለጹት ሃላፊው ÷ የማልማትና ምርታማነትን የማሳደግ አቅም መኖሩን አመልክተዋል፡፡
በክልሉ የግብርና ክላስተር ልማት ተጠናክሮ መቀጠሉንና ከአምራች ኢንዱስተሪው ጋር በማስተሳሰር የተሰናሰለ ልማት እንዲሁም ቀጣይነት ያለው እድገት ለማምጣት እየተሰራ ይገኛል ነው ያሉት፡፡
በክልሉ ከለውጡ በኋላ የተጀመሩ አዳዲስ የግብርና ልማት ኢንሸቲቮችን ጨምሮ በኢንቨስትመንት፣ ኢንዱስትሪ፣ ማዕድንና ቱሪዝም ዘርፎችም ያልተነካ አቅም መኖሩን አውስተዋል፡፡
ስለሆነም ሃብቱን በተቀናጀ መልኩ የማልማት ሥራ ልዩ ትኩረት የተሰጠው መሆኑን አቶ ኃይለማሪያም ለፋና ዲጂታል ገልጸዋል፡፡
ክልሉ ለኢንቨስትመን አገልግሎት የሚሆን ምቹ አከባቢ በመሆኑ ወደ ክልሉ ለሚመጡ አልሚ ባለሃብቶች አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግ አብራርተዋል፡፡
በክልሉ የሚገኙ ከተሞችን ፅዱና አረንጓዴ በማድረግ ለነዋሪዎች ምቹ እንዲሆኑ የክልሉ መንግሥት በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡
በክልሉ አሁን ላይ በ18 ከተሞች የኮሪደር ልማት ሥራ እየተከናወነ ሲሆን÷ የግብርናም ይሁን የከተሞችን ልማት በማስተዋወቅ ረገድ መገናኛ ብዙሃን ሚናቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።