Fana: At a Speed of Life!

አቶ ሽመልስ በክላስተር የታረሰ የእርሻ ማሳን ጎበኙ

አዲስ አበባ ፣ ነሃሴ 15፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ የተመራ ልዑክ በምዕራብ አርሲ ዞን ሻሸመኔ ወረዳ በክላስተር የታረሰ የቦሎቄ ማሳ ጎበኙ።
 
አርሶ አደሮቹ ከዚህ ቀደም በተበታተነ መልኩ ይሰራ የነበረውን አሰራር በመተው በክላስተር መስራት በመጀመራቸው ከአንድ ሄክታር እስከ 30 ኩንታል ለማግኘት ተስፋን ሰንቀው እንዲጠባበቁ እንዳስቻላቸው ለተሳታፊ ልዑኩ ተናግረዋል ።
 
በወረዳው አሁን ላይ 8 ሺህ 556 ሄክታር መሬት በቦሎቄ ክላስተር መሸፈኑን የምዕራብ አርሲ ዞን እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ በሪሶ ፈይሳ ገልፀዋል ።
 
በተመሳሳይ ልዑኩ በዶዶላ ወረዳ በክላስተር የታረሱ የምግብና ቢራ ገብስ እንዲሁም የስንዴ የእርሻ ማሳን ጎብኝቷል።
 
በክላስተር የታረሰው 10 ሺህ ሄክታር የምግብ ገብስ እና 8 ሺህ ሄክታር የቢራ ገብስ ሙሉ በሙሉ ሲሆን በ18 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ያረፈው ስንዴ ደግሞ 60 በመቶው በክላስተር የታረሰ መሆኑን አቶ በሪሶ ፈይሳ ተናግረዋል።
 
በዚህም በሄክታር 50 ኩንታል ስንዴ ፣ 35 ኩንታል የምግብ ገብስ እና 60 ኩንታል የቢራ ገብስ ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል።
 
የአካባቢው አርሶ አደሮችም በክላስተር መስራት ውጤታማ እያደረጋቸው እንፈሚገኝ ነው የተናገሩት።
 
በተጨማሪም ልዑኩ በዞኑ በሻላ ወረዳ ተገኝቶ በሁከትና ብጥብጡ ወቅት ወድመው አሁን ላይ በመንግሥት እና በህዝብ ተሳትፎ ዳግም እየተገነቡ ያሉ የመኖሪያና የንግድ ተቋማትን ጎብኝቷል ።

በአዳባ ከተማ አስተዳደርም  16 መኖሪያ ቤቶች እና 2 ሄቴሎች ጥቃት ተፈፅሞባቸው የነበረ ሲሆን  በህብረተሰቡ እና በመንግስት ተሳትፎ 12 መኖሪያ ቤቶች ጥገና እንደተደረገላቸው የከተማዋ ከንቲባ አቶ ሙስጠፋ ዑመር ተናግረዋል ።

በርዕሰ መስተዳድሩ የሚመራው ልዑክ በተመሳሳይ በባሌ ዞን በምትገኝ አጋፋ ወረዳ ጉዳት የደረሰባቸው የመንግስት ተቋማትን የጎበኘ ሲሆን አቶ ሽመልስ አብዲሳ ከህብረተሰቡ ጋር በነበራቸው ቆይታ የመልሶ ማቋቋም ስራው በአፋጣኝ እንደሚጀምር ገልፀዋል።

በነበራቸው ቆይታ አብዛኛው ውድመት የደረሰበት የመንግስት ተቋም ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ህዝቡ እራሱ መልሶ እንዲገነባው አቅጣጫ አስቀምጠዋል፡፡

ህብረተሰቡም ጉዳት አድራሾቹን በአፋጣኝ አጋልጦ እንዲሰጥ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በወረዳው 38 የመንግስት ተቋማት መውደማቸው ታውቋል፡፡

በትዝታ ደሳለኝ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.