የተቀናጀና በጥናት ላይ የተደገፈ መፍትሔ የሚጠይቀው የፍልሰት ጉዳይ…
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 11፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የፍልሰት ችግርን በዘላቂነት ለመፍታት ተቋማዊ ትብብርና በጥናት ላይ የተደገፈ ምላሽ መስጠት ይገባል አሉ የትምህርት ሚኒስቴር አማካሪ ሚኒስትር ዴኤታ ክንደያ ገ/ህይወት (ፕ/ር)፡፡
ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር በፍልሰት ጉዳይ ላይ ያተኮረ የመጀመሪያውን ዓለም አቀፍ የምርምር ኮንፈረንስ አካሂዷል።
ክንደያ ገ/ህይወት (ፕ/ር) በመድረኩ ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት፥ ፍልሰትን በአግባቡ ለማስተዳደር የሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብ እንደሚስፈልግ ተናግረዋል።
የፍልሰትን አሳሳቢነት ከግንዛቤ በማስገባት የትምህርት ሚኒስቴር በቅርቡ ባዘጋጀው ሀገራዊ የምክክር መድረክ ላይ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በጉዳዩ ላይ የተሻለ አማራጭ ለመጠቆም የሚያስችላቸውን ጥናት እንዲያካሂዱ አቅጣጫ መቀመጡን አስታውሰዋል፡፡
ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ይህንን ኃላፊነት ለመወጣት ግንባር ቀደም በመሆን ባዘጋጀው ኮንፈረንስ ላይ በፍልሰት ዙሪያ ትልቅ ትኩረት ለሚያስፈልጋቸው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አካባቢዎች አማራጭ ሀሳብ እንደሚያቀርብ እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡
ሕጋዊ ፍልሰት ግለሰባዊና ሀገራዊ ጥቅም ማግኘት እንደሚያስችል ጠቁመው፥ ነገር ግን በህገወጥ ፍልሰት የሚከሰቱ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ተቋማዊ ትብብርና በጥናት ላይ የተደገፈ ምላሽ መስጠት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ካሰች ኤሊያስ በበኩላቸው፥ ሕገወጥ ፍልሰትን በዘላቂነት ለመፍታት ከሚመለከታቸው አጋር ተቋማት ጋር እየተሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡
መንግስታዊ ተቋማት ከበጀታቸው 2 ነጥብ 5 በመቶ ሕገወጥ ፍልሰትን ለመከላከል እንዲያውሉ በመስተዳድር ምክር ቤት ደንብ መጽደቁን ተናግረዋል።
በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዚዳንት ዘውድነህ ቶማስ (ዶ/ር) እንዳሉት፥ በክልሉ የሚገኙት የወላይታ፣ አርባምንጭ፣ ዲላና ጂንካ ዩኒቨርሲቲዎች በመተባበር በፍልሰት ጉዳይ ጥናትና ምርምር እያካሄዱ ይገኛሉ፡፡
ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱ በተጨማሪ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ባለድርሻ አካላት በጋራ የሚያከናውኗቸው መሰል ተግባራት የፍልሰትን አረዳድ በመቀየር ተጠቃሚነትን የሚያሳድግ ነው ብለዋል።
በመለሰ ታደለ