Fana: At a Speed of Life!

በግብርና ዘርፍ ያለውን የፋይናንስ አቅርቦት ችግር ለመፍታት እየተሰራ ነው – መለስ መኮንን (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 13፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በግብርና ዘርፍ ያለውን የፋይናንስ አቅርቦት ችግር ለመቅረፍ በትኩረት እየተሰራ ነው አሉ የግብርና ሚኒስትር ዴዔታ መለስ መኮንን (ዶ/ር)፡፡

ሚኒስትር ዴዔታው ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷ ግብርና በኢትዮጵያ ለአብዛኘው ሕዝብ የሕይወት መሰረት በመሆኑ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት የሚፈልግ ዘርፍ ነው፡፡

ይሁን እንጂ በዘርፉ ለሚንቀሳቀሱ አነስተኛ አርሶ አደሮችና ባለሃብቶች የሚቀርበው የግብርና ፋይናንስ አጅግ አነስተኛ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡

ለችግሩ እልባት ለመስጠትም ለዘርፉ የሚቀርበውን ብድር ከማሳደግ ባለፈ በኢንሹራንስ እንዲደገፍ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡

ኢንሹራንስና የብድር አቅርቦት ተቀናጅተው መስራት ከቻሉ በሁሉም ዘርፍ አመርቂ ውጤት ማምጣት እንደሚቻል አመልክተዋል፡፡

ከፍተኛ የሥራ እድል የሚፈጥረውንና የኢኮኖሚ መሰረት የሆነውን ግብርና ይበልጥ ለማሳደግና ለማዘመንም የፋይናንስ አቅርቦትን ማሳለጥ እንደሚያስፈልግ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

ስለሆነም ባንኮችን ጨምሮ ሁሉም የፋይናንስ ተቋማት ለአርሶ አደሩና በዘርፉ ለተሰማሩ ባለሃብቶች ብድር እንዲያቀርቡ የሚያስገድድ ብሄራዊ የግብርና ፋይናንስ አቅርቦት ፍኖተ ካርታ መዘጋጀቱን አብራርተዋል፡፡

ፍኖተ ካርታው ባንኮች ከዚህ በፊት ለግብርና ይሰጡት የነበረውን ብድር በማሳደግ የዘርፉን ምርታማነት ማጠናከር ያስችላል ነው ያሉት፡፡

ባንኮች እና ሌሎች የፋይናንስ ተቋማት ለግብርናው ዘርፍ ስንት በመቶ ብድር መስጠት አለባቸው የሚለው ላይ ውይይት እየተደረገበት እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡

ፍኖተ ካርታው በተለይም የወጪ ንግድና ሌሎች ምርቶችን በጥራት፣ መጠንና አይነት በማሳደግ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት እንደሚያግዝ አስገንዝበዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.