Fana: At a Speed of Life!

የሀገር በቀል ማህበራት ሚና ኤችአይቪን ለመከላከልና መቆጣጠር..

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 15፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሀገር በቀል ማህበራትን ተሳትፎ ማሳደግ ለኤችአይቪ (ኤድስ) መከላከልና መቆጣጠር ወሳኝ ሚና አለው አለ የጤና ሚኒስቴር፡፡

ሀገር አቀፍ የኤችአይቪ፣ ሄፓታይተስና የአባላዘር በሽታዎች ፕሮግራም የ2018 ዓ.ም መጀመሪያ ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ በሃዋሳ ተካሂዷል፡፡

የሲዳማ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ሰላማዊት መንገሻ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷የኤችአይቪ ፕሮግራም ዓለም አቀፍ ድጋፍ እየቀነሰ በመሆኑ ዜጎች ለአደጋ እንዳይጋለጡ የሀገር በቀል ማህበራትን ሚና ማጠናከር ይገባል፡፡

በተለይም የሃብት አሰባሰቡን ማሳደግና የተገኘውን ገቢ በአግባቡ ጥቅም ላይ ማዋል ግዴታ መሆኑን ተናግረዋል።

በሚኒስቴሩ የኤችአይቪ መከላከል መሪ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ፈቃዱ ያዴታ በበኩላቸው÷ በማሕበረሰቡ ዘንድ የሚታየው መዘናጋት፣ የፋይናንስ ድጋፍ መቀነስና የሚሰጠው ትኩረት ማነስ የዘርፉ ተግዳሮቶች እንደሆኑ አስረድተዋል፡፡

ስለሆነም ያለንን የካበተ ልምድ እና አቅም በማቀናጀት ወደ ተሻለ ምዕራፍ መሸጋገር አለብን ነው ያሉት፡፡

የሀገር አቀፍ ኤችአይቪ በደማቸው የሚገኝ ማህበራት ጥምረቶች ጥምረት (የኔፕ +) ዳይሬክተር አቶ ካሳሁን ታደሰ÷ ባለፉት ዓመታት በኤችአይቪ መከላከልና መቆጣጠር ለተመዘገበው ውጤት ቫይረሱ በደማቸው የሚገኝባቸው ወገኖች ከፍተኛ ሚና ነበራቸው ብለዋል፡፡

በቀጣይም ተሳትፏቸውን ይበልጥ ማጠናከር አስፈላጊ ነው ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

እንደ ሀገር አሁን ላይ የኤችአይቪ (ኤድስ) ሥርጭት ምጣኔ 0.85 በመቶ ሲሆን ÷ አዲስ አበባ (3.14%) ፣ ጋምቤል (3.09%) ፣ ሐረሪ (2.65%) እና ድሬዳዋ (2.22%) ከፍተኛ የኤችአይቪ ስርጭት ምጣኔ ያለባቸው መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.