የቡና አምራች አርሶ አደሮችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሰራ ነው – አቶ አዲሱ አረጋ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 21፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የቡና አምራች አርሶ አደሮችን ተጠቃሚነት የሚያረጋገጡ የማሻሻያ ስራዎች እየተሰሩ ነው አሉ የግብርና ሚኒስትሩ አዲሱ አረጋ፡፡
በሚኒስትሩ የተመራ ቡድን በሲዳማ ክልል ተገኝቶ የቡና ልማት እንቅስቃሴን ጎብኝቷል።
በዚህ ወቅት አቶ አዲሱ አረጋ እንዳሉት፤ በተያዘው በጀት ዓመት 600 ሺህ ቶን ቡና ለውጭ ገበያ በማቅረብ ከ3 ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር በላይ ለማግኘት ታቅዷል።
በአርሶ አደሩ እና በህብረት ስራ ማህበራት አማካኝነት እየለማ ያለው ቡና ዕቅዱን ለማሳካት እንደሚያስችል ጠቅሰው፤ በሲዳማ ክልል የታየው የቡና ልማት ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።
ቡና አምራች አርሶ አደሮች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል የተለያዩ የማሻሻያ ርምጃዎች እየተወሰዱ እንደሆነ ገልጸው፤ ለአብነትም አርሶ አደሮች በቀጥታ ለውጭ ገበያ ምርት እንዲልኩ የሚያስችል ሁኔታ መፈጠሩን ተናግረዋል።
አርሶ አደሮቹ በቡና ስፔሻሊቲ ላይ ግንዛቤያቸው እንዲያድግ መደረጉን እና በቀላሉ ፈቃድ የሚያገኙበት አሰራር መዘርጋቱን አብራርተዋል፡፡
በዓለም ገበያ በጣዕሙ ልዩ የሆነ ቡና የምታቀርበው ኢትዮጵያ በሚገባት ልክ እንድትጠቀም ተጨማሪ ስራዎች ያስፈልጋሉ ነው ያሉት።
የሲዳማ ክልል እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ መምሩ ሞኬ በበኩላቸው÷ በክልሉ የቡና ምርታማነትን ለማሳደግ ክላስተር በማደራጀት አርሶ አደሩ በህብረት እንዲሰራ እየተደረገ ነው ብለዋል።
የክልሉ ቡና፣ ፍራፍሬና ቅመማ ቅመም ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር መስፍን ቃሬ÷ ክልሉ በበጀት ዓመቱ 40 ሺህ ቶን ቡና ለማዕከላዊ ገበያ እንደሚያቀርብ ገልፀዋል፡፡
በጥላሁን ይልማ