Fana: At a Speed of Life!

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በሕዳርና ታሕሣሥ ወራት ያከናወኗቸው ቁልፍ ተግባራት…

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሕዳር እና ታሕሣሥ ወር 2018 ዓ.ም ቁልፍ የሆኑ ተከታታይ ሀገራዊ፣ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ተግባራትን አከናውነዋል።

ሁሉም ክንውኖች የኢትዮጵያን ተፈላጊነት እና ተጽዕኖ ፈጣሪነት በጽኖ መሠረት ላይ ያስቀመጡ ናቸው።

የህንድ ሪፐብሊክ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ለይፋዊ የስራ ጉብኝት ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸውን ተከትሎ፥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ያካሄዱት የሁለትዮሽ ውይይት እና በሀገራቱ መካከል የተደረሰው ሁሉን አቀፍ ስምምነት ትልቅ ትርጉም ተሰጥቶታል።

የመሪዎቹ ውይይት በዋናነት በንግድ እና ኢንቬስትመንት፣ በዲጂታይዜሽን እና ቱሪዝም ያለውን ትብብር በኢትዮጵያ እና ህንድ መካከል ወደላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ያለመ ነው።

በተጨማሪም በሁለቱ ሀገራት መካከል በጉምሩክ የጋራ አስተዳደር ድጋፍ፣ በኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዳታ ማዕከል ምስረታ የመግባቢያ ሥምምነቶች እንዲሁም በዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ላይ ያላቸውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ እና የሚያጠናክር የተባበሩት መንግሥታት የሰላም ማስከበር ሥራ የመግባቢያ ሥምምነት ፊርማ የተከናወነበት ነው። አንዲሁም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) እና ጠቅላይ ሚኒስትር ሞዲ በፓርላማ ተገኝተው የህንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር በየኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የጋራ ስብሰባ ላይ ንግግር አድርገዋል።

አህጉራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ፥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከአፍሪካ እና ቀጠናዊ አጋሮች ጋር በመገናኘት ተወያይተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ፀሃፊ ክላቨር ጋቴቴ ጋር እ.ኤ.አ በ2027 አፍሪካን በሚገባ የሚወክል ኮፕ 32 በማዘጋጀት ረገድ ከኢትዮጵያ ጋር በጋራ ስለሚሰሩባቸው መንገዶች ውይይት አካሂደዋል።

በተመሳሳይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ህብረት አህጉሪቱን በሚገባ የሚወክል ጉባኤ ለማዘጋጀት እንዴት ተቀራርበው መስራት እንደሚችሉ አስቻይ ሁኔታዎችን ለመፍጠር፥ ከአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር እና ከቡድናቸው ጋር ተወያይተዋል። በውይይቱም ኮፕ 32ን (COP32) የተሳካ ለማድረግ የኢትዮጵያ ቁልፍ አጋርነት እና አፍሪካዊ መፍትሄ ስለሚጠናከርበት መንገድ ተነስቷል።

በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሶማሊያ ፌደራል ሪፐብሊክ ፕሬዝደንት ሀሰን ሼኽ መሐሙድን እና የኬንያውን ፕሬዝዳንት ዊልያም ሩቶን ለሥራ ጉብኝት ወደ ኢትዮጵያ በመጡበት ወቅት ተቀብለው አነጋግረዋል።

ከሁለቱ መሪዎች ጋር የነበረው ውይይት በዋናነት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች በሚጠናከርበት ሁኔታ ላይ ያጠነጠነ ነበር። እንዲሁም በአፍሪካ ቀንድ ሰላም እና ፀጥታ ጉዳዮች ላይ መሪዎቹ ሃሳብ የተለዋወጡ ሲሆን፤ ይኽም በሰላም እና መረጋጋት፣ ንግግር ብሎም በአፍሪካ መር መፍትሔዎች ላይ ያላቸውን የወል ጽኑ አቋም አጽንኦት የሰጠ ነበር።

በሀገር ውስጥ ጉዳዮች ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ የታለመለትን ግብ አሳክቶ በመጠናቀቁ፤ ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 በይፋ አስጀምረዋል።

ይህ ስትራቴጂክ ፕሮግራም ተደራሽነትን ማስፋት፣ ለዜጎች እኩል እድል መፍጠር እንዲሁም በዜጎችና ተቋማት መካከል መተማመንን ማጎልበት ቁልፍ እና መሰረታዊ ትልሞቹ ሆኖ ወደ ትግበራ ገብቷል። በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 በተለይ የህዝብ ዲጂታል መሠረተ ልማትን ማስፋት ላይ ትልቅ ስራ የሚከናወን ሲሆን፣ ይህም ዲጂታል ቴክኖሎጂ ሰው ተኮር ሆኖ የዜጎችን ኑሮ እንዲያሻሽል ትልቅ አቅም ይፈጥራል።

በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) እንደገለጹት፥ በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 የተቀመጡ ግቦች እንዲሳኩ ሁለት መሠረታዊ አስቻይ ጉዳዮች እንዳሉ ጠቁመዋል። አንደኛው የኤሌክትሪክ ተደራሽነት ነው ያሉ ሲሆን፤ የኤሌክትሪክ ተደራሽነት የዲጂታል ቴክኖሎጂ ምግብ ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል ብለዋል።

ሁለተኛው ደግሞ የኢንተርኔት ትስስር ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በርካታ ከተሞች የኢንተርኔት ትስስር ተጠቃሚ እንደሆኑ ተናገረዋል። ነገር ግን በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ይህን ትስስር በሁሉም አካባቢዎች ሙሉ ለሙሉ ተደራሽ ማድረግ እንዳለበትም አጽንኦት ሰጥተዋል። በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ የሞባይል ተጠቃሚ ደንበኞች ቁጥር 128 ሚሊዮን የሚደርስ ሲሆን፣ የ5ጂ ኔትወርክ ሽፋንን 100 ከተሞች ይደርሳል ይጠበቃል።

በአጠቃላይ በዲጂታል ኢትዮጵያ የሚከናወኑ ስራዎች የመደመር መንግስት በቀለለ ቢሮክራሲ ታላላቅ ስትራቴጂዎችን እውን ለማድረግ ከያዘው ግብ ጋር የተሳሰሩ ናቸው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)።

በሌላ በኩል የ20ኛው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን በዓል በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በውቢቱ ሆሳዕና ከተማ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች በተገኙበት በደማቅ ሁኔታ ተከብሯል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በበዓሉ ባደረጉት ንግግር “የኢትዮጵያን ችግሮች ብቻ ሳይሆን አቅሞቿን መመልከት ይገባናል” ብለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው፥ “አንድ ክር ደካማ ነው፤ ብዙ ክር ግን የማይበጠስ ገመድ ይፈጥራል። ስንበዛና ስንሰናሰል በቀላሉ የማንበጠስ ስለምንሆን፤ መተባበር፣ በጋራ መቆምና ብሔራዊ ጥቅም ማስከበር የሁላችን ስንቅ ሊሆን ይገባል ሲሉ በዕለቱ ተደምጠዋል። በሚቀጥለው ዓመትም የጅማ ከተማ 21ኛውን በዓል እንደምታከብርም በፕሮግራሙ ላይ ተገልጿል።

በጥቅሉ ህዳር እና ታህሳስ ወር የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አመራር ኢትዮጵያ በሀገር ውስጥ ዘመናዊነትን በማሳለጥ፤ በአህጉር እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ ስትራቴጂካዊ ዲፕሎማሲዋን በማጠናክር ረገድ ያላትን ቁረጠኝነት ያረጋገጠችበት ነው። በዚህም የዲጂታል አካታችነትን በማጎልበት፣ ቀጠናዊ አጋርነትን በማሳደግ እና ዓለም አቀፍ ትብብርን በማጠናከር፤ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፋዊ ከፍተዋን አጽንታለች።

#PMOEthiopia

ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation

Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting

Facebook https://web.facebook.com/fanasport

Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate

Telegram t.me/fanatelevision

Website www.fanamc.com

TikTok www.tiktok.com/@fana_television

WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29

Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment

TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment

Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.