ገናን በላሊበላ …
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 24፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ላሊበላ ከተማ ለኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል (ገና) አስፈላጊውን ዝግጅት አጠናቅቃ የበዓሉ ታዳሚ እንግዶችን እየተቀበለች ነው፡፡
በኢትዮጵያ በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት ከሚከበሩ ኃይማኖታዊ በዓላት መካከል የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል (ገና) አንዱ ነው።
የገና በዓል በልዩ ሁኔታ በድምቀት የሚከበርባት የላሊበላ ከተማም በዓሉን በስኬት ለማክበር አስፈላጊውን ዝግጅት አጠናቅቃ እንግዶችን መቀበል ጀምራለች፡፡
የላሊበላ ከተማ ከንቲባ አቶ መሳይ ወዳጄ እንደሚሉት ÷ የገና በዓልን በላሊበላ ለማክበር የሚመጡ የውጭና የሀገር ውስጥ እንግዶች አይረሴ ጊዜን እንዲያሳልፉ አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል፡፡
በተለይም እንግዶች በቆይታቸው የበዓሉን አከባበር እና ሌሎች ሁነቶችን በሚገባ እንዲረዱ ትኩረት ተደርጎ መሰራቱን አስረድተዋል፡፡
ለአብነትም ከአንድ አለት የተፈለፈሉ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን ጨምሮ በአካባቢው የሚገኙ ሌሎች መዳረሻዎችን ለማስጎብኘት ዝግጅት ተደርጓል ነው ያሉት፡፡
ሆቴሎችና ሌሎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ኢትዮጵያዊ የእንግዳ አቀባበል እሴትን ባንጸባረቀ መልኩ የበዓሉ ታዳሚዎችን ተቀብለው እያስተናገዱ እንደሚገኙ አውስተዋል፡፡
ከትራንስፖርት ጋር ተያይዞ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ገናን በላሊበላ የሚታደሙ መንገደኞችን ብዛትና ፍላጎት መሠረት በማድረግ የበረራ ቁጥሩን ማሳደጉን ተናግረዋል፡፡
የአማራ ክልል ባህል ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አበበ እምቢያለ በበኩላቸው÷ እንግዶች ገናን በላሊበላ ለማክበር ባለፉት ቀናት ወደ ከተማዋ መግባት መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡
እስካሁን ድረስም 13 ሺህ የሚጠጉ የሀገር ውስጥ እና የውጭ እንግዶች ወደ ከተማዋ መግባታቸውን ነው የገለጹት፡፡
እንግዶች ላሊበላ ከተማ ሲደርሱም የከተማዋ ወጣቶችና ነዋሪዎች የእንግዶችን እግር በማጠብና በመንከባከብ እየተቀበሉ እንደሚገኙ ለፋና ዲጂታል ገልጸዋል፡፡
እንግዳን እግርን አጥቦ መቀበልና ማስተናገድ የላሊበላ ባህል ሲሆን÷ በአካባቢው የፍቅር ማሳያና የትሕትና መገለጫ ከሆኑ ትልልቅ ተግባራት አንደኛው ነው፡፡
እንግዶች በዓሉን አይረሴ በሆነ መልኩ በድምቀት አክብረው እንዲመለሱ የአካባቢው ሕብረተሰብ አስፈላጊውን ትብብር እያደረገ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል፡፡
በሌላ በኩል ሆቴሎች፣ አስጎብኚ ድርጅቶችና ሌሎች ተቋማት ለውጭና ሀገር ውስጥ እንግዶች የዋጋ ጭማሪ ሳያደርጉ ከዚህ በፊት በነበረው ዋጋ እንዲሰጡ የተደረሰውን ስምምነት እየተገበሩ ነው ብለዋል፡፡
ለሆቴል ባለሙያዎችና አስጎብኚ ድርጅቶች እንግዶችን በምን መልኩ ማስተናገድና ማስጎብኘት እንዳለባቸው ሥልጠና መሰጠቱን ነው አቶ አበበ አስታውሰዋል፡፡
ስለሆነም የውጭና የሀገር ውስጥ እንግዶች የኢየሱስ ክርስቶስን የልደት በዓል በላሊበላ ተገኝተው እንዲያከብሩና አይረሴ ጊዜን እንዲያሳልፉ ጥሪ ቀርቧል፡፡
በመላኩ ገድፍ