የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ከአንድ ሚሊየን በላይ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ተሳትፈዋል
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 15፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል እስካሁን ከአንድ ሚሊየን በላይ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ተሳታፊ መሆናቸውን የሴቶች፡ ሕፃናትና ወጣቶች ሚኒስቴር አስታወቀ።
የሴቶች፡ ሕፃናትና ወጣቶች ሚኒስትር ዲኤታ ወይዘሮ ሕይወት ኃይሉ በሃገሪቱ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል በሚደረገው ዘመቻ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ግንባር ቀደም ተሳታፊዎች መሆናቸውን ተናግረዋል።
ወጣቶቹ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል በጤና ባለሙያዎች የሚቀርቡ የመከላከያ ሥልቶችን ለማኅበረሰቡ የማስተዋወቅ፣ የማስተማርና ንቅናቄ የመፍጠር ሥራ እየሰሩ መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡
ወጣቶቹ ለቫይረሱ እንዳይጋለጡ ከጤና ሚኒስቴርና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅርብ እየተሰራ መሆኑንም ሚኒስትር ዲኤታዋ ገልጸዋል።
በሌላ በኩል ወጣቶች ጊዜያቸውን በአግባቡ ለመጠቀምና ራሳቸውን ለመለወጥ የሚያስችሉ ማዕከላትን መልሶ የማቋቋም ሥራ እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች በተያዘው የ10 ዓመት መሪ ዕቅድ የወጣቶች ጉዳይ ትልቅ ትኩረት እንደተሰጠው ኢዜአ ዘግቧል።