በሶማሌ ክልል በዚህ ዓመት 700 ሺህ ዜጎችን የፋይዳ መታወቂያ ባለቤት ማድረግ ተችሏል
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 26፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በሶማሌ ክልል በዚህ ዓመት 700 ሺህ ዜጎችን የፋይዳ መታወቂያ ባለቤት ማድረግ ተችሏል አሉ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ኢብራሂም ኡስማን፡፡
”ፋይዳ ለኢትዮጵያ” በሚል መሪ ቃል በጅግጅጋ ከተማ ሁለተኛው ዙር የፋይዳ ኢትዮጵያ የ5 ኪሎ ሜትር የሩጫ ውድድር ተካሂዷል።
አቶ ኢብራሂም ኡስማን በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፥ በክልሉ በዚህ ዓመት 3 ሚሊየን ለሚሆኑ ዜጎች የፋይዳ መታወቂያ ተደራሽ ለማድረግ ታቅዶ እየተሰራ ይገኛል፡፡
እስካሁን 700 ሺህ ዜጎች የፋይዳ መታወቂያ ባለቤት ማድረግ መቻሉን ገልጸው፥ በቀጣይም ያለወሰዱ ዜጎች መታወቂያውን በመውሰድ የጥቅሙ ተጋሪ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል።
የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ዋና አስተባባሪ ዩዳሄ አርአያስላሴ በበኩላቸው፥ ውድድሩ የፋይዳ መታወቂያ እሴቶችን ለማስተዋወቅና ለማስረፅ ፋይዳው የላቀ ነው ብለዋል፡፡
በውድድሩ ላይ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ አትሌቶች፣ ታዋቂ ግለሰቦችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተሳተፉ ሲሆን፥ ከ1ኛ እስከ 3ኛ ላጠናቀቁ ተወዳዳሪዎች ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
በተስፋዬ ኃይሉ