Fana: At a Speed of Life!

ምርጫ ለሀገር ግንባታና ሰላም መጽናት ዋና መድረክ በመሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዝግጁ ሊሆኑ ይገባል – የሰላም ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 26፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሰላም ሚኒስትር መሃመድ ኢድሪስ ምርጫ ለሀገር ግንባታና ሰላም መጽናት ዋና መድረክ በመሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለመጪው ምርጫ ዝግጁ ሊሆኑ ይገባል አሉ፡፡

የሰላም ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ “ሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ለሰላማዊ ምርጫ” በሚል መሪ ሀሳብ ከፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ጋር ምክክር አድርጓል።

አቶ መሃመድ ኢድሪስ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ መጪው ምርጫ ውጤታማ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የፖለቲካ ፓርቲዎች የበኩላቸውን ሚና መወጣት ይኖርባቸዋል።

ምርጫ ሀገርና ህዝብ ወዳድነት የሚገለጥበት መድረክ መሆኑን ጠቅሰው፥ የፖለቲካ ፓርቲዎች በዚህ መንፈስ ዝግጁ ሊሆኑ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

ስልጣን በጉልበት ከሚያዝበት ያለፈው ዘመን አውድ በመውጣት በፖለቲከኞችና በህዝብ መካከል ውል ማስቀመጫ መድረክ መሆኑንም አንስተዋል።

ምርጫ የሰው ልጅ የፖለቲካ እድገትና ስልጣኔ ማሳያ መድረክ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፥ ለትውልድ የሚተርፍ ሀገር መፍጠር የሚቻለውም ስልጡንና ዴሞክራሲን በተከተለ መስመር በሚከወን ምርጫ መሆኑን አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ሰሎሞን አየለ በበኩላቸው፥ የፖለቲካ ፓርቲዎች አሁናዊ እንቅስቃሴ ዓለምአቀፋዊ ተለዋዋጭ ኑባሬዎችን የተገነዘበ ሊሆን እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች በተለይም መጪው ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የጎላ ሚና እንዳላቸው በመገንዘብ ሊንቀሳቀሱ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

ይህንን ሚና በአግባቡ በመወጣት ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ስነ ምህዳር የሰፋበትን የፖለቲካ አውድ ማስፋት ይቻላል ነው ያሉት።

በይስማው አደራው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.