የቢሾፍቱ አውሮፕላን ማረፊያ በግንባታ ሂደት ላይ ከሚገኙ የዓለማችን ግዙፍ ፕሮጀክቶች አንዱ ሆነ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 26፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የቢሾፍቱ አውሮፕላን ማረፊያ በግንባታ ሂደት ላይ ከሚገኙ የዓለማችን ግዙፍ የአውሮፕላን ማረፊያ ፕሮጀክቶች ዝርዝር ውስጥ ተካትቷል፡፡
ኮንስትራክሽን ብሪፊንግ የተሰኘ ድረገፅ የፕሮጀክቶቹን የግንባታ ወጪ፣ የሚያስተናግዱትን የበረራ ቁጥርና የበረራ ተርሚናል መስፈርት በማድረግ በግንባታ ላይ ያሉ 15 የዓለማችን ግዙፍ የአውሮፕላን ማረፊያ ፕሮጀክቶችን ይፋ አድርጓል፡፡
በዚህም መሰረት የቢሾፍቱ አውሮፕላን ማረፊያን ጨምሮ የአውስትራሊያው ፕሪዝ፣ የህንዱ ኖይዳ እንዲሁም የአሜሪካዎቹ ሳንፍራንሲስኮ እና ሳን ዲያጎ አውሮፕላን ማረፊያዎች በዚህ ዝርዝር ውስጥ ከተካተቱ ግዙፍ ፕሮጀክቶች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡
ድረገፁ ባወጣው ዝርዝር መረጃ የቢሾፍቱ አውሮፕላን ማረፊያ በቴክኖሎጂ፣ በዲዛይን፣በተርሚናል ቁጥር ከሌሎች ዓለምአቀፍ አውሮፕላን ማረፊያዎች ጋር የሚኖረው ትስስር ከዓለማችን ግዙፍ አውሮፕላን ማረፊያዎች አንዱ እንዲሆን ያስችለዋል ብሏል፡፡
ፕሮጀክቱ በርካታ ኩባንያዎችን፣ የቴክኒክ አማካሪዎችን፣ የምህንድስና ባለሙያዎች የፕሮጀክት አስተዳደር ባለሙያዎችና ተቆጣጣሪዎችን ያካተተ መሆኑንም ጠቅሷል፡፡
ዛሃ ሀዲድ አርክቴክትስ እና ዳር አል ሀንዳሳህ የተባሉ የፕሮጀክት አማካሪዎች የግንባታውን የማማከር ስራ እንደሚያከናውኑ አመላክቷል፡፡
የአውሮፕላን ማረፊያው የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታ በፈረንጆቹ 2029 ሲጠናቀቅ በዓመት 60 ሚሊየን መንገደኞችን የሚያስተናግድ ሲሆን፥ ቀጣይ የግንባታ ምዕራፍ ተጠናቆ በሙሉ አቅሙ ሥራ ሲጀምር በዓመት እስከ 110 ሚሊየን የተለያዩ ሀገራት መንገደኞችን የማስተናገድ አቅም ይኖረዋል፡፡
ይህ አቅም በአፍሪካ ትልቁ አውሮፕላን ማረፊያ የሚያደርገው ሲሆን፥ የዲዛይን ስራው ቀደም ሲል መጠናቀቁ ተገልጿል፡፡
የአውሮፕላን ማረፊያው ኢትዮጵያ የአህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ የአቪዬሽን መግቢያ በር የመሆን አቅሟን ከማጠናከር ባሻገር ለቀጣናዊና አህጉራዊ ትስስር ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ይታመናል፡፡
የፕሮጀክት ዕቅዱ የአየር መንገዱ ዋና ስራ አስፈፃሚ መስፍን ጣሰው፣ የአፍሪካ ልማት ባንክና የዳር አል ሀንዳሽ የፕሮጀክት አማካሪ ተወካዮችና ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ይፋ መደረጉ ይታወሳል፡፡
ዋና ስራ አስፈጻሚው በዚህ ወቅት እንደገለጹት÷ በግንባታው ከ40 በላይ የሀገር ውስጥና የውጭ ተቋማት ይሳተፋሉ፡፡
አውሮፕላን ማረፊያው ለኢትዮጵያኢኮኖሚ ከሚያበረክተው በከፍተኛ አስተዋጽኦ ባሻገር ለአፍሪካ ጥሩ ብስራት ይሆናል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።
የአውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ፕሮጀክት የማስጀመሪያ ስነስርዓት በቅርቡ ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎች በተገኙበት ይከናወናል፡፡
በሚኪያስ አየለ