Fana: At a Speed of Life!

የባቡር መንገድ ግንባታ ላይ የተመዘገበው ዕድገት አስደናቂ ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 26፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በውስጣዊ እና በራስ ዐቅም የባቡር መንገድ ግንባታ ላይ የተመዘገበው ዕድገት እጅግ የሚያስደንቅ ነው አሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በዛሬው ዕለት የኢትዮ ጅቡቲ ምድር ባቡር አክሲዮን ማህበርን መጎብኘታቸውን በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው አስፍረዋል፡፡

ጉብኝቱ የሀገራችንን ብሔራዊ የሎጂስቲክስ ክዋኔ ዐቅም ለመገምገም እና የሀገሪቱን እያደገ ያለ የልማት አጀንዳ ለመደገፍ በሎጂስቲክስ ዝግጁነት ላይ ገንቢ ውይይቶችን ለማካሄድ ጠቃሚ ዕድል ሰጥቶናል ብለዋል።

ኢኮኖሚያችን እያደገ ሲሄድ የሎጂስቲክስ ዘርፉ ካልዘመነ ዘላቂ ዕድገትን የሚገድብ ዋና መሰናክል ይሆናል ነው ያሉት፡፡

አሁን በተለይም በውስጣዊ እና በራስ ዐቅም የባቡር መንገድ ግንባታ ላይ የተመዘገበው ዕድገት እጅግ የሚያስደንቅ ነው ሲሉ አስረድተዋል።

ይህም የሀገር ውስጥ ዐቅምን ለመገንባት፣ ውጤታማነትን ለማሻሻል እና በባቡር ዘርፍ ውስጥ ረጅም ጊዜ የሚቆይ ዘላቂነትን ለማረጋገጥ ያለንን ጽኑ ቁርጠኝነት ያሳያል ብለዋል።

ሎጂስቲክስ ከባሕር እስከ መጋዘኖች ድረስ ያለውን ሙሉ ሰንሰለት ያካተተ መሆኑን ገልጸው÷ ይህም ወደቦች፣ የባቡር መንገዶች፣ አውራ ጎዳናዎች፣ የትራንስፖርት አገልግሎቶች እና የማከማቻ ተቋማትን ይጨምራል ነው ያሉት።

በአሁኑ ወቅትም በእጃችን ውስጥ ባሉ መስኮች ላይ እንደ ደረቅ ወደቦች፣ የባቡር መሠረተ ልማት፣ አውራ ጎዳናዎች እና የመጋዘን ግንባታ አስፈላጊ ማሻሻያዎችና ዘመናዊ የማድረግ ሥራዎች በሒደት ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

እነዚህን ተያያዥ የሎጂስቲክስ ክፍተቶችን በተቀናጀ መንገድ መፍታት የዘርፉን መሰናክሎች ለመሻር እና የሀገሪቱን ሰፊ የልማት ግቦች ለመደገፍ ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.