Fana: At a Speed of Life!

ሚኒስቴሩ ቅሬታ እና ጥቆማ ማቅረብ የሚያስችል ሥርዓት ይፋ አደረገ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 28፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የገቢዎች ሚኒስቴር ቅሬታን እና ጥቆማን ማቅረብ የሚያስችል ሥርዓት ይፋ አድርጓል።

የጥቆማ እና ቅሬታ ማቅረቢያ ሥርዓቶቹን ይፋ ያደረጉት የገቢዎች ሚኒስትር ዓይናለም ንጉሴ እና የሚኒስቴሩ የኢ-ዳታ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዳዊት ውብሸት ናቸው፡፡

በዚህም 6844 ነፃ የጥሪ መስመር እና ጥቆማ ማቅረቢያ ሥርዓት በመጠቀም ማንኛውንም የገቢውን ዘርፍ አሠራሮችን በተመለከተ ጥቆማ መቀበል የሚያስችል ነው ተብሏል።

በአዲሱ ሥርዓት ባለጉዳዮች ከተቋሙ ሰራተኞች ሥነ-ምግባር ጋር የተያያዘ ወይም በማንኛውም አገልግሎት ላይ ቅሬታ ሲኖራቸው ያለ ምንም ክፍያ ለማቅረብ የሚያስችል ነው፡፡

ባለጉዳዮች ቅሬታ ወይም ጥቆማ ሲያቀርቡ የሥነ-ምግባር መከታተያ ዳይሬክቶሬት ሠራተኞችን በቀጥታ ማግኘት እንደሚያስችል እና በሥራ መደራረብ ምክንያት ስልኩ ባይነሳ እንኳን ሠራተኞቹ ያልተነሳውን ጥሪ አይተው ወደ ባለጉዳዮች በመደወል ጥቆማውን መቀበል እንደሚችሉ ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡

ተገልጋዮች ማንነታቸውን ገልጸውም ይሁን ሳይገልጹ ቅሬታቸውን ማቅረብ የሚችሉ ሲሆን ለጉዳዩ ለአቅራቢዎቹ የሚሰጣቸውን መከታተያ ቁጥር በመጠቀም የቅሬታቸውን ሂደት መከታተል እንደሚችሉ ነው የተጠቀሰው፡፡

ሌላኛው ይፋ የተደረገው የቅሬታ ማቅረቢያ ፖርታል ሲሆን ሥርዓቱ የገቢዎች ሚኒስቴርን እና ጉምሩክ ኮሚሽንን በተመለከተ የተለያዩ ቅሬታዎችን ማቅረብ የሚስችል መሆኑን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

በፖርታሉ የግብር ማስያዣን በተመለከተ፣ የዘገየ ተመላሽ ገንዘብ፣ ኢ-ፍትሃዊ ቅጣቶች፣ የምዝገባ ጉዳዮች፣ የሁለቱን ተቋማት አጠቃላይ አሠራሮችን እንዲሁም ሌሎች አገልግሎቶች ላይ ያሉ ቅሬታዎች መቅረብ እንደሚያስችል በመረጃው ተመላክቷል፡፡

#ኢትዮጵያ #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.