Fana: At a Speed of Life!

ምሁርነት ለጥያቄ ዝግጁ መሆንና የመጠየቅ ብቃት ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 26፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ምሁርነት ለጥያቄ ዝግጁ መሆን እና የመጠየቅ ብቃት ነው አሉ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ያሉት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ 75ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ላይ ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፍ ነው።
ዩኒቨርሲቲ መግባት ለምሁርነት አንድ ርምጃ ወደ ፊት የሚያራምድ ቢሆንም ለዘላለም ዩኒቨርሲቲ ውስጥ መቆየት ግን ምሁር አያሰኝም ብለዋል፡፡
ምሁር የሚባለው ከአንድ ዲፓርትመንት ባሻገር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ሃሳብ መስጠት እና ማስተናገድ ሲችል ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ከአንድ ዲፓርትመንት በመውጣት በማሕበረሰብ ውስጥ ጠብ የሚል ነገር ማበርከት ሲችል ምሁር ይባላል ብለዋል፡፡
የማሕበረሰብ አንቂዎች፣ የሃሳብና የተቋማት መሪዎች የሚማማሩ ከሆነ ቀና ብለን እንድንራመድ ማድረግ ይችላሉ ሲሉም አስረድተዋል፡፡
የእነዚህ አካላት ዋናው ጉዳይ ለለውጥ ክፍት ያልሆነን ማሕበረሰብ አዳዲስ ነገርን እንዲማርና እንዲቀበል ማስተማር መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
የማሕበረሰብ አንቂዎች ለለውጥ ዝግጁ የሆነ ማሕበረሰብ ለመፍጠር ኃላፊነት እና የአመራር ሚና እንደሚጠበቅባቸው ጠቁመዋል፡፡
የሃሳብ መሪዎች የሚገበያዩት በሃሳብ መሆኑን ጠቅሰው፥ ይህንን በደንብ የማያውቅ አመራር ግን ያሰበውን ማሳካት አይችልም ብለዋል፡፡
የሃሳብ መሪዎች በፈጠራ እና በተቀየረ የልቦና ውቅር ሰውን ለዘመን ማዘጋጀት ትልቁ ስራቸው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን እየገጠመን ያለው ችግር በእጃችን ላይ ያለውንና ኃላፊታችንን አለማወቅ ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡
እጃችን ላይ ያለውን ሀብት ማወቅ ለሁሉም ነገር ትልቅ መፍትሄ መሆኑን ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጽሑፋቸው ያመላከቱት፡፡
በወንድማገኝ ፀጋዬ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.