Fana: At a Speed of Life!

ሁለንተናዊ እድገትን ለማምጣት ገቢር ነበብ የለውጥ ሒደትና የተባበረ አቅም ያስፈልጋል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 26፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ሁለንተናዊ እድገትን ለማምጣት ገቢር ነበብ የለውጥ ሒደትና የተባበረ አቅም ያስፈልጋል አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ 75ኛ ዓመት የምሥረታ በዓልን አስመልክተው “የምሁራን ሚና ለሀገራዊ ብልጽግና” በሚል ርዕስ ጥናታዊ ጽሑፍ አቅርበዋል፡፡
በዚህም የለውጥ እድል በሁለት አጣብቂኝ መካከል በሚል ያልተሻገርነው እና የሚመጣው በሚል ሃሳብ ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በማብራሪያቸውም ባለንበት ዘመን እድልና አጣብቂኝ መኖሩን ጠቅሰው÷ ይሕንን አጣብቂኝ መሻገር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
እንደ ሀገር የጋራ የሚያግባባ እውነት ሳንፈጥር ዓለም ወደ ድህረ እውነት መሸጋገሩንና የጋራ የሆነ እውነት ባልፈጠሩ ሀገራት ዓለም እየሄደ ያለበት ርቀት በጣም አሳሳቢ መሆኑን ጠቅሰዋል።
እኛ ውሸት የሆነ መረጃን መረዳት ሳንችል ዓለም ስር የሰደደ የውሸት መረጃ ላይ መሸጋገሩን ጠቅሰው÷ ስር የሰደደ የውሸት መረጃ ማለት መረጃው ውሸት ስለመሆኑ እንኳን ለመለየት የሚያስቸግር እንደሆነ አስረድተዋል።
የጋራ የሆነ እውነትን ፈጥረን፣ ለለውጥ ክፍት ሆነን ዓለም እየተጓዘበት ያለበትን ፍጥነት ማየት ካልቻልን የገባን መስሎን ሳይገባን ዘመን ያልፋል ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል።
አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ የሰውን ልጅ ስራ ያሳጣል፣ይጋራል በሚባልበት ዘመን እኛ ሞፈርና ቀንበር መጣል የከበደንና በትራክተር እንኳን ማረስ በቅጡ ያልተለማመድን መሆኑ ሁለተኛው ያልተሻገርነው የለውጥ እድል ነው ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ልዩነትን ከግጭት ውጪ ባሉ አፈታቶች በሰላምና ንግግር ማየት ከእኛ ባህል ውጪ ሆኗል ሲሉም አንስተዋል።
ይህም በንግግር እየተቃረንን በጋራ መቆም እንዳንችል ማድረጉንና ያልተሻገርነው ሌላኛው ስጋት እንደሆነ አመልክተዋል።
የሥነ ምህዳር አጥር እንዳለብን አንስተው ÷ እንደ ትልቅ ሀገር ሌሎች ከተመኙት እኛስ ለምን አንመኝም የሚለው ጉዳይ ላይ ለመወያየት ያለን ፍቃደኝነት ምን ያህል ነው ሲሉም ጠይቀዋል።
“እኔ የቀይ ባህር ጉዳይ አያገባኝም፣ይህ የኔ ጥያቄ አይደለም” የሚሉ ፖለቲከኛ ነን ባዮችን ማየት ብቻ የምናስበውን ለማሳካት ያለብንን ውስንነት የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡
ከዚህም ለመሻገር የተሻገረ ብሄራዊ ራዕይ፣ ገቢር ነበብ የለውጥ ሒደት፣ የተባበረ የለውጥ አቅምና ሃይል ያስፈልገናል ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡
የወረት እና የጊዜ ውስንነት ፣ ያለፈው እዳና የነገው ስጋት አጣብቂኝ ስላለብን በከፍተኛ ደረጃ ብሄራዊ ራዕይ ኖሮን ለዚያ መትጋት ይጠበቅብናል ሲሉ አሳስበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ መጪውን ጊዜ እና ነባራዊ ሁኔታን ያገናዘበ ራዕይ፣ አዲስና የጠራ እሳቤዎችን የሚያስተናግድ ዐውድ እንደሚስፈልግም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
በሶስና አለማየሁ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.