Fana: At a Speed of Life!

ሚድሮክ በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን ዓለም አቀፍ ግዙፍ የችርቻሮ ንግድ አስተዋወቀ

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 28፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በሚድሮክ ኢትዮጵያ ስር የሚገኘው ኩዊንስ ሱፐርማርኬት በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን ዓለም አቀፍ ግዙፍ የችርቻሮ ንግድ አስተዋውቋል፡፡

ኩዊንስ ሱፐርማርኬት ከዓለም አቀፉ የችርቻሮ ንግድ ተቋም ካርፎር ጋር በኢትዮጵያ የዘመናዊ ችርቻሮ ንግድ ዘርፍ ዕድገት ላይ ትልቅ ለውጥ የሚፈጥር የንግድ ስያሜን ከነሙሉ አሰራሩ የመጋራትና የአቅርቦት አጋርነት መመሥረቱን አስታውቋል፡፡

በስምምነቱ መሠረት ኩዊንስ ሱፐርማርኬት የካርፎርን ስም እና ዓርማ፣ የኩባንያውን የችርቻሮ ንግድ ዕውቅት እና ዓለም አቀፍ የአሠራር መስፈርቶችን በኢትዮጵያ በሚገኙ የሱፐርማርኬት ቅርንጫፎቹ ላይ ተግባራዊ ያደርጋል።

በዚህ አጋርነት የመጀመሪያው ዓለም አቀፍ ግዙፍ የችርቻሮ ንግድ ፍራንቻይዝ ለኢትዮጵያ ገበያ የተዋወቀበት ሲሆን ይህም በኢትዮጵያ ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት የሚደግፍ ስለመሆኑም ተመላክቷል።

የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ጀማል አህመድ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ ስምምነቱ የሀገር ውስጥ ምርትን ከዓለም አቀፍ የንግድና የጥራት ደረጃዎች ጋር በማጣጣም፣ የኢትዮጵያ ምርቶች ዓለም አቀፍ መስፈርቶችን እንዲያሟሉና በውጭ ገበያ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ዕድል የሚከፍት ነው፡፡

ስያሜያቸውን ወደ ካርፎር የሚቀይሩ የመጀመሪያዎቹ የኩዊንስ ሱፐርማርኬቶች በመጪው ሰኔ ወር አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምሩ አንስተዋል።

የካርፎር ኢንተርናሽናል ፓርትነርሺፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፓትሪክ ላስፋርጉስ በበኩላቸው በኢትዮጵያ ግንባር ቀደም ከሆነ የችርቻሮ ንግድ ተቋም ጋር ትብብር በመጀመራችን ደስተኞች ነን ብለዋል።

እስከፈረንጆቹ 2028 ድረስ 17 ተጨማሪ የችርቻሮ መደብሮችን ለመክፈት መታቀዱንም ተናግረዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.