Fana: At a Speed of Life!

በዓለም ላይ የገና በዓል የሚከበርባቸው ዕለታት…

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 28፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በተለያዩ የዓለም ሀገራት በድምቀት ከሚከበሩ በዓላት መካከል የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በዋናነት ይጠቀሳል።

ታሕሣሥ 16 ቀን በርካታ ሀገራት የገናን በዓል ያከበሩ ሲሆን÷ ኢትዮጵያን ጨምሮ የተለያዩ ሀገራት ደግሞ ታሕሣሥ 29 ያከብሩታል።

በልደት በዓል አከባበር ዙሪያ የተፈጠረው የቀናት ልዩነትም የተጀመረው በ1582 ዓ.ም በሮማ ካቶሊክ መሪ በፖፕ ጎርጎርዮስ 13ኛ ምክኒያት መሆኑን መጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ (ዶ/ር) ከፋና ዲጂታል ጋር ባደረጉት ቆይታ ተናግረዋል።

ይኸውም ጎርጎርዮስ የዮልዮስ የዓመት ብዛት 365 ቀን ከ6 ሰዓት የሚለውን 365 ቀን ከ5 ሰዓት ከ48 ደቂቃ ከ46 ሴኮንድ መሆን አለበት በማለት ጥቅምት 4 ቀን 1582 ዓ.ም ላይ ቀጣዩ ቀን ጥቅምት 5 ሳይሆን ጥቅምት 15 መሆን አለበት የሚል ውሳኔ በማስተላለፋቸው እንደሆነ አስረድተዋል።

በዚህ ምክንያት የ10 ቀን ልዩነት መፈጠሩን ያነሱት መጋቤ ሐዲስ ሮዳስ (ዶ/ር)÷ ይህም የዘመን አቈጣጠር ጎርጎርዮሳዊ የዘመን ቀመር በመባል እንደሚታወቅ ይገልጻሉ።

ውሳኔውም የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ባለባቸው ሀገራት ፈጥኖ ተቀባይነት ማግኘቱን ገልጸው÷ በምሥራቅ አውሮፓ ሀገራት ዘግይተው በ1923 ዓ.ም አካባቢ መቀበላቸውን ጠቁመዋል፡፡

በአብያተ ክርስቲያናት ደረጃ ፖፕ ጎርጎርዮስ የጨመሯቸው 11 ዕለታት አስቀድሞ ተቀባይነት ያገኘው በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በመቀጠል ደግሞ የፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮች በበዙበት ሀገራት እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

በዚህም በ1582 ዓ.ም ውሳኔው ሲተላለፍ በሮማ ካቶሊክ ስር የነበሩት ጣሊያን፣ ፈረንሳይ፣ ፖላንድ፣ ስፔን፣ ፖርቹጋል እና ሉግዘምበርግ ወዲያው እንደተቀበሉ እና ከዚያ በኋላ የተለያዩ ሀገራት ቀስ በቀስ ውሳኔውን እየተቀበሉ መምጣታቸውን ገልጸዋል።

ይሁን እንጂ በሮማ ካቶሊክ መሪ በፖፕ ጎርጎርዮስ 13ኛ የተላለፈው ውሳኔ በምሥራቅ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ ተቀባይነት አለማግኘቱን መጋቤ ሐዲስ ሮዳስ (ዶ/ር) አብራርተዋል፡፡

በመሆኑም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን ጨምሮ በኢየሩሳሌም የግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን፣ የሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን፣ የሰርቢያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን፣ የጆርጂያ ኦርቶዶክስና ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን፣ የፖሊሽ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን እና የመቄዶንያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ውሳኔውን አይቀበሉትም።

በዚህም እነዚህ አብያተ ክርስቲያናት ዛሬም ድረስ የልደት ወይም የገና በዓልን ታሕሣሥ 29 ቀን እንደሚያከብሩ አስረድተዋል፡፡

በዮናስ ጌትነት

ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation

Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting

Facebook https://web.facebook.com/fanasport

Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate

Telegram t.me/fanatelevision

Website www.fanamc.com

TikTok www.tiktok.com/@fana_television

WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29

Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment

TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment

Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.