Fana: At a Speed of Life!

‘በገና ጨዋታ አይቆጡም ጌታ’ የገና ባህላዊ ጨዋታ …

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 28፣2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ባህላዊ እና ሀይማኖታዊ ይዘት ያለው የገና ጨዋታ ከኢየሱስ ክርስቶስ ልደት በሁዋላ የሚዘወተር ትውፊታዊ ክዋኔ እንደሆነ ታሪክ ያስረዳል።

ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር ቆይታ ያደረጉት መመህር ዘበነ ለማ÷ የኢየሱስ ክርስቶስ ልደትን ምክንያት በማድረግ እረኞች የገና ጨዋታን ከታሕሣሥ ጀምሮ እስከ ጥር ከዚያም እስከ ክረምቱ መግቢያ ድረስ ይጫወቱት እንደነበር ይናገራሉ፡፡

የገና ጨዋታ ባህላዊም ሀይማኖታዊም መሆኑን ጠቅሰው÷ በኢትዮጵያ የገና ጨዋታ በይበልጥ መዘውተር እና መስፋፋት የጀመረው በ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መባቻ መሆኑን አውስተዋል፡፡

ከልጅ አስከ አዋቂ፣ ከእረኛ እስከ ዳኛ፣ ከሎሌ እስከ ጌታ ሳይለይ ሁሉም በአንድነት ላይ የመጫወት መብት እንዳለው በመጥቀስ፤ ሌላው ቀርቶ መኳንንቱና መሳፍንቱ ራሱ በረከቱ እንዳይቀርብን እያሉ ይጫወቱ ነበር ብለዋል።

የኢትዮጵያ ባህል ስፖርት ፌዴሬሽን የገና ታሪካዊ ዳራ በሚል ባሳተመው ፅሁፍ÷ በአንድ ወቅት የአጼ ምኒልክና የእቴጌ ጣይቱ ቡድኖች በፍል ውኃ ሜዳ ከቀትር በኋላ ግጥሚያ አድርገው እንደነበር ያስረዳል፡፡

ንጉሡና ንግሥቲቱ ቡድናቸውን ሲያበረታቱ ውለው ጀምበር ለዓይን ስትይዝ ጨዋታው በእቴጌ ጣይቱ ቡድን አሸናፊነት ተጠናቀቀና አሸናፊው ቡድን ወዲያው ሆታ በመጀመር እንዲህ ሲል ተሸናፊውን የምኒልክን ቡድን ማብሸቅ ጀመረ፡፡

እጅ የለውም ወይ እጅ የለውም ወይ፣
የምኒልክ ቡድን ሩር አይለጋም ወይ፣
ብርሌውን ብድግ ጠጁን ዶቅዶቃ፣
የምኒልክ ቡድን ፍል ውኃ ተወቃ፡፡
የምኒልክ ቡድንም በመሸነፉ አዝኖ ሌሊቱን ሁሉ እንዴት ማሸነፍ እንደሚችል ሲያሰላስል ካደረ በኋላ በማግሥቱ በዚያው ሜዳ ላይ ለግማሽ ቀን በተደረገ ጨዋታ የምኒልክ ቡድን ረታ፡፡ ከዚያም የምኒልክ ቡድን በተራው “አራሽ ባየሽ የኛ ጣይቱ፣ አፍሽን በዳበሽ” … በማለት የንግሥቲቱን ቡድን እንዳበሸቋቸው ይነገራል፡፡

በገና ጨዋታ ጊዜ ሴቶች በቀጥታ ተሳታፊ ባይሆኑም ጨዋታው በሚካሄድበት ቦታ ዳር ቆመው ግጥም በመግጠምና በማዜም ያበረታታሉ፡፡ በወንዶች በኩል ግን የእድሜና የስልጣን ገደብ የለም፡፡

በጨዋታው ሎሌና ጌታ ሳይቀሩ ይሳተፉ ስለነበርና በሚደርሰውም አደጋ ቂም መያያዝ ስላልነበረ እንዲህ ተብሎ ይዘፈን ነበር፡-

በገና ጨዋታ የለም ሎሌ ጌታ
በገና ጨዋታ አይቆጡም ጌታ፡፡

የገና ጨዋታ ጉልበትና አቅም የሚጠይቅ ብቻም ሳይሆን ጥንቃቄ ካላደረግን በአካል ላይም ጉዳት ሊያስከትል የሚችል መሆኑ ቀድሞ የታወቀ በመሆኑ በጨዋታው ወቅት ጥርሴ ረገፈ፣ እጄ ተሰበረ፣ እግሬ ተሰበረ፣ ራሴ ተፈነከተ፣ ዓይኔ ጠፋ … ወዘተ ብሎ ክስና ቂም የለም፡፡

ማድረግ የሚቻለውና ብቸኛው መፍትሔ ቢኖር ተፎካካሪ ወገንን በጥሩ የግጥም ስንኝ እንደፈለጉ ‹‹ማብሸቅ›› ብቻ ነው። በገና ጨዋታ ሩር መታሁ ብሎ መሳት አሊያም እግር መምታት የተለመደ ነው፡፡ በዚህ ጊዜ ደግሞ የሚከተለው ማብሸቂያ ግጥም ይገጠማል፡፡

ሩር መታሁ ብሎ እግሩን ጠረገና፣
ተሸከሙኝ አለ ዘራፉ ቀረና፡፡

የገና ጨዋታ በከፍተኛ ሁኔታ የሚካሄደው መኸር በተሰበሰበበት አካባቢ ለጥ ባለ ሜዳ ላይ ከሰዓት በኋላ ሩሯ ለዐይን መታየት እስከቻለችበት ጊዜ ድረስ ነው።

ጨዋታው የሚካሄደው በሁለት የቡድን አባቶች አማካኝነት እያንዳንዱ ተወዳዳሪ የተለየ ስም እየያዙ፣ ትከሻ ለትከሻ በመያያዝ ለሁለቱ የቡድን አባቶች እያቀረቡና ስም እያስመረጡ ወደ ቡድናቸው ይቀላቀላሉ።

ይህም የሚሆነው ሁለቱ ቡድኖች ከአንድ መንደር ወይም ከአንድ ቀበሌ ከሆኑ ብቻ ነው። ሌላው ከፍተኛ የውድድር ዓይነት ደግሞ በሁለት የቡድን አባቶች የተመደበ ደብር ከደብር፣ የላይ አምባ ከታች አምባ፣ የአንዱ ቀበሌ ከሌላው ቀበሌ ተከፍለው የጨዋታውን ዓይነት በስምምነት የሚፈፀም ሲሆን የልግ ልውውጥ ይደረጋል።

የገና ጨዋታ መጫወቻ በትር ከጫፉ ቆልመም ያለ ሲሆን ‘ገና’ ተብሎ የሚጠራ ሲሆን፤ የመጫወቻ ኳሱ (ጥንግ ወይም ሩር) ደግሞ ድቡልቡል ከሆነ የዛፍ ስር እና ከጎማ ይሰራል።

የገና ጨዋታ ዛሬ በዓለም ዘንድ በጣም ተፈላጊ ከመሆን ደረጃ አልፎ ተርፎ በኦሊምፒክ ከሚደረጉት ውድድሮች አንዱ ለመሆን በቅቷል።

በሚኪያስ አየለ

ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation

Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting

Facebook https://web.facebook.com/fanasport

Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate

Telegram t.me/fanatelevision

Website www.fanamc.com

TikTok www.tiktok.com/@fana_television

WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29

Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment

TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment

Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.