የገና በዓል የውጭና የሀገር ውስጥ ታዳሚዎች በተገኙበት በላሊበላ ከተማ በድምቀት ተከበረ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 29፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል (ገና) በርካታ ምዕመናን፣ የውጭና የሀገር ውስጥ ታዳሚዎች በተገኙበት በላሊበላ ከተማ በድምቀት ተከብሯል።
የሰሜንና ደቡብ ወሎ እንዲሁም የከሚሴ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብጹዕ አቡነ ኤርምያስን ጨምሮ ሌሎች ሊቃነ ጳጳሳትና እንግዶች ከበዓሉ ዋዜማ ጀምሮ እስከ ቤዛ ኩሉ ሥነ ሥርዓት ታድመዋል።
በበዓሉ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ÷ መንግሥት ለላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ጥበቃና እንክብካቤ በማድረግ ቅርሱ ዘመን ተሻጋሪ እንዲሆን እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ታሪካዊ ቅርሶችንና እሴቶችን ከመጠበቅና ከመንከባከብ ጎን ለጎን የኢትዮጵያን ትንሳኤ እውን ለማድረግ በጋራ ለልማት መትጋት ይገባልም ነው ያሉት።
የጥንት አያቶችን ህያው ቅርሶችና ትውፊቶች በመጠበቅና አዲስ ታሪክ በመስራት አሰባሳቢ ትርክት መገንባት ከዛሬው ትውልድም ይጠበቃል ብለዋል።
የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ስለሺ ግርማ በበኩላቸው÷ መንግሥት ቅርሶችን ከመጠበቅና ከመንከባከብ ባለፈ አዳዲስ መዳረሻዎችን በማልማት ለቱሪዝም ዘርፉ እድገት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በርካታ ቅርሶች በዩኔስኮ በዓለም ቅርስነት በማስመዝገብ ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸው÷ የገና በዓል በላሊበላ በድምቀት መከበሩ ቅርሱን ለመላው ዓለም ለማስተዋወቅ ፋይዳው የላቀ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በበዓሉ ላይ የተገኙት የተለያዩ ሊቀ ጳጳሳትም ኢትዮጵያ ሰላሟና አንድነቷ ጸንቶ እንዲኖር ህዝቡ አንድነት፣ ፍቅርና አብሮነቱ ማጠናከርና ለሰላሙ ተግቶ ሊሰራ እንደሚገባ አመልክተዋል።
የእየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል (ገና) በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ይገኛል።