Fana: At a Speed of Life!

የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ከቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 30፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ማህሙድ አሊ ዩሱፍ ከቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ይ ጋር ተወያይተዋል።
ሁለቱ ወገኖች አፍሪካና ቻይና በዘመናዊነት፣ በዓለም አቀፍ አስተዳደር፣ በዜሮ ታሪፍ አያያዝ እንዲሁም በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና ልማት ላይ ያላቸውን ትብብር በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ ነው የተወያዩት።
አፍሪካ እና ቻይና በተለያዩ ዘርፎች ላይ በሚያደርጉት ትብብር ዙሪያ ሐሳባቸውን የተለዋወጡት ሊቀመንበሩና ሚኒስትሩ÷ የአፍሪካ ሕብረትና ቻይና በዋና ዋና ዓለም አቀፍ እና አሕጉራዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ሰጥተው እንደሚሰሩ ጠቁመዋል።
ሁለቱ ወገኖች መብቶቻቸውንና ጥቅሞቻቸውን ለማስጠበቅ እና እርስ በእርስ ለመደጋገፍ ያላቸውን ቁርጠኝነትም አረጋግጠዋል።
በዚህም ለዓለም አቀፍና ቀጣናዊ ሰላም፣ ለልማት እንዲሁም አዎንታዊ እድገትን ለማዳበር በሁለቱ ወገኖች መካከል ያለውን ቅንጅታዊ ትብብር ይበልጥ ማጠናከር እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።
የተፈረሙ የትብብር ስምምነቶች እና የመግባቢያ ሰነዶች ውጤታማ በሆነ መንገድ ተግባራዊ እንዲሆኑ ለማድረግም ያላቸውን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።
በአፍሪካ ሕብረት እና በቻይና መካከል ያሉ ሁለንተናዊ ትብብሮች የአፍሪካ እና ቻይና ሕዝቦችን ጥቅም ባስጠበቀ መልኩ መቀጠል እንዳለበትም አጽንዖት ሰጥተዋል።
ሊቀመንበሩ እና ሚኒስትሩ ከውይይቱ ጎን ለጎን የአፍሪካ እና ቻይና የ2026 የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ፕሮግራምን በይፋ አስጀምረዋል።
በሶስና አለማየሁ
ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment
Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.