Fana: At a Speed of Life!

የሰማዩ መርከቦች …

አዲስ አበባ፣ ጥር 4፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ የሆነ፣ የአፍሪካ የፓን አፍሪካኒስቶች መታያ እንዲሁም የመቻል ትዕምርት የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ የምድራችን አድማስ እየሰነጠቀ የአየር ትራንስፖርቱ መተማመኛ ነው።

አንጋፋ የማስታወቂያ ባለሙያ የነበሩት ጋሽ ውብሸት ወርቅለማሁ” የኢትዮጵያ አየር መንገድ ያልተቆጠበ ጥረቱ፣ ደንበኞቹ እንዲደሰቱ…” ያሏት የማስታወቂያ ስንኝ የትናንት ጥረቱ የዛሬ እና የነገን ከፍታውን ለክተው የተስፈነጠሩ ይመስላሉ።

ትጋት ከፍጥነት እና ፈጠራ ጋር አኮብኩበው የኢትዮጵያ አየር መንገድን ከቦሌ ወደ ቢሾፍቱ በፈጣን ባቡር ወስደውታል። ግዙፍ ለአፍሪካ፣ ለዓለም ደግሞ ከጥቂቶቹ እንደ አንዱ የሚሆነው የአቡሴራ አውሮፕላን ማረፊያ የኢትዮጵያን ታላቅነት ዳግም ሊገልጥ የመሠረተ ድንጋይ ተቀምጧል።

ይህም የኢትዮጵያ ድሎች በጉባ ምርቃት ብቻ የደስታ ፈንጠዝያ አጀንዳው ወደ ጠረጴዛው መሳቢያ የገባ የመሰላቸውን ቢያስደነግጥም ቅሉ ለወዳጆቿ ደግሞ ታላቅ ብስራት ሆኗል። ዓለም በዚህ ሰዓት በጂኦ ፖለቲካዊ አዲስ የኃይል አሰላለፍ ፍትጊያ ሲባትል ኢትዮጵያ ግን ሥራ ላይ ናት።

ከዓባይ እስከ ቀይ ባሕር የጉባ ብስራቶቿን ፍጥነት ለመቀነስ በየቀኑ የሚጠላለፉትን ድሮች ኢትዮጵያ በሥራ በመቀየር ለአፍሪካ አብነት፣ ለዓለም ደግሞ ግንባር ቀደም ተመራጭ አየር መንገድ የመሆኗን እውነት እያጸናች ትገኛለች።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግን 80 ዓመታት በትውልድ ቅብብሎሽ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ኩራት ሆኖ የዘለቀ የኛ ኃብት፤ በአንድ ቃል የአሸናፊነት ካባ በየአቅጣጫው የተደረበለት ተቋም ነው።

አየር መንገዱም ከኢትዮጵያውያን የትናንት፣ የዛሬ ታሪክ እና የነገ ሕልሞች ጋር እንደ ስጋና ደም የተዋደደ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። ከኬፕታውን እስከ ካይሮ፣ ከቶኪዮ እስከ ኮፐንሀገን የዓለም ሕዝብ ቀና ብሎ እንዲመለከተው ያደረገ ክብሩን እና ዝናውን የጠበቀ ተቋም ሲሉ መወድስ ያወጡለታል።

የመሠረተ ድንጋዩን ያስቀመጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በወቅቱ ባደረጉት ንግግር የአየር መንገዱን ሠራተኞች ከሀገር ጠበቂ ወታደር ጋር አመሳስለው፤ ለኢትዮጵያ ሰንደቅ ክብር ሁሌም በትጋት የቆሙ፣ ለአዲስ እውቀትና ቴክኖሎጂ ቀድመው የሚገኙ፤ የሚታጠቁ ናቸው ሲሉ አውስተዋል፡፡

የዓለም አየር መንገዶች ከፍታና ዝቅታቸውን እንደ መዳፉ ያውቃል የሚባልለት የሲኤንኤን የአቪዬሽን ዘርፍ ሊቅ ሪቻርድ ኩዌስት በአንድ ወቅት፤ “የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዓለም ላይ ቀዳሚ ከሚባሉት አንዱ ነው። ሰዎች በሌሎች አየር መንገዶች ስጋት ሲገባቸው በኢትዮጵያ አየር መንገድ እበራለሁ የሚሉት አይነት አየር መንገድ ነው” በማለት መመስከሩ አይዘነጋም።

ዛሬ ላይ ከ160 በላይ ዘመናዊ አውሮፕላኖች፣ ከ145 በላይ በሚሆኑ መዳረሻዎች፣ በዓመት 25 ሚሊየን መንገደኞችን በምቾት እና እምነት እያንፈላሰሰ ከምኞታቸው ስፍራ የሚያደርሰው ይህ አየር መንገድ እዚህ ጋር ደግሞ ሌላ ነገን የመዋጀት በረራ በበረራ ቁጥር 7 ወደ ቢሾፍቱ በሯል።

ከ7ቱ የጉባ ብስራቶች ወደ ተግባር የተቀየረው አንዱ የሆነው የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በላቀ እቅድ በዓመት 110 ሚሊየን መንገደኞችን ለማስተናገድ በአቡሴራ የግንባታውን የታሪክ ገጽ -1 በማለት ጀምሯል።

አሁን በቢሾፍቱ 130 ሚሊየን ሕዝብን የሚመጥን በሰማይ ላይ ለሚበሩ መርከቦች የወደብ ሥራ ተጀምሯል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ የኢትዮጵያውያን የአየር ላይ ወደባቸው ሆኖ ሰንደቃችን በብሔራዊ ክብር ከፍ እንዳደረገ ይበራል።

በኃይለኢየሱስ መኮንን

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.