ግብርናውን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር …
አዲስ አበባ፣ ጥር 6፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት የግብርናውን ዘርፍ ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር በትኩረት እየሰራሁ ነው አለ።
ከተቋቋመ 15 ዓመት የሆነው ኢንስቲትዩቱ በግብርና ዘርፍ ዕድገት ያበረከተውን አስተዋጽኦ አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።
የኢንስቲትዩቱ ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ብሩክታዊት እጅጉ (ዶ/ር) በወቅቱ እንዳሉት፤ ምርታማነትን በመጨመር የግብርና ትራንስፎርሜሽንን እዉን ለማድረግ በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል።
ኢንስቲትዩቱ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ የዘርፉን ማነቆዎችን በጥናት በመለየት እና አዳዲስ ፕሮጀክቶችን በመተግበር ከፍተኛ አዎንታዊ አስተዋጽኦ አድርጓል ብለዋል።
በዚህም የግብርና ትራንስፎርሜሽንን እውን ለማድረግ ቴክኖሎጂን በመጠቀም፣ ትስስሮችን በማጠናከር፣ ቅንጅትን በማሳለጥ እና ጠንካራ አጋርነትን በማጎልበት አመርቂ ውጤት መመዝገቡን ተናግረዋል።
አነስተኛ ይዞታ ያላቸውን አርሶ አደሮች ኑሮ ለማሻሻል እና የግብርናውን ዘርፍ ለመቀየር የሚያስችሉ ከ400 በላይ የሚሆኑ ጥናቶች ተካሂደው 80 በመቶ ያህሉ ወደ ተግባር መቀየራቸውን አመልክተዋል።
አቅምን በመገንባት እና የፈጠራ ፕሮጀክቶችን በመምራት ረገድ ውጤት መገኘቱንም ተናግረዋል።
በግብርና ኮሜርሻላይዜሽን ክላስተር መርሐ ግብር በዘጠኝ ክልሎች በሚገኙ 311 ወረዳዎች አነስተኛ ይዞታ ያላቸው አርሶ አደሮች በእሴት ሰንሰለት አቀራረብ ምርታቸውን ለገበያ ማቅረብ እንዲችሉ መደረጉን አብራርተዋል።
ኢንስቲትዩቱ የግብርና ግብአቶችንና ቴክኖሎጂዎችን ለአርሶ አደሩ በማቅረብ ጉልህ አስተዋጽኦ አበርክቷል ነው ያሉት።
በ748 ወረዳዎች የማሣዎችን ባህሪ በማጥናት የአፈር ማዳበሪያ ፍላጎታቸው መለየቱን ጠቅሰው፤ ከዚህ ቀደም የነበረው የአፈር ማዳበሪያ ስርጭት ልምድ መቀየሩን አመልክተዋል።
የዓለም ምግብ እና እርሻ ድርጅት (ፋኦ) በፈረንጆቹ 2019 ባጠናው ጥናት ኢንስቲትዩቱ ከምስረታው ጀምሮ ለኢትዮጵያ ጠቅላላ ሀገራዊ ምርት የ1 ነጥብ 7 ቢሊየን ዶላር አስተዋጽኦ ማድረጉን እና 286 ሺህ አርሶ አደሮች ከድህነት ማላቀቅ መቻሉን ማረጋገጡን ብሩክታዊት እጅጉ (ዶ/ር) በመግለጫቸው አስረድተዋል።
አደይ የተሰኘ ግብርና ተኮር የወጣቶች የስራ ዕድል ፈጠራ ፕሮግራም በመተግበር የወጣቶችን ሕይወት የሚያሻሽሉ አካታች ሥራዎችም እየተሰሩ እንደሆነ አንስተው፤ በፕሮግራሙ ከ200 ሺህ በላይ ወጣቶች ስራ አግኝተዋል ብለዋል።
በሶስና አለማየሁ