በሰው ሰራሽ አስተውሎት የሚታገዙ የሬዲዮ ኔትዎርኮች…
አዲስ አበባ፣ ጥር 6፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ የሚታገዙ የሬዲዮ ኔትዎርኮች ለአፍሪካ የቴሌኮም ኦፕሬተሮች ቀጣዩ የቴክኖሎጂ ምዕራፍ እየሆኑ መጥተዋል።
የአፍሪካ የቴሌኮም ኩባንያዎች የዳታ ፍጆታ መጨመርና የላቀ የዲጂታል አገልግሎት ፍላጎትን ለማሟላት በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የሚታገዙ የሬዲዮ ግንኙነት ኔትዎርኮችን ተግባራዊ እያደረጉ ነው።
ይህ ዘዴ ማሽን ለርኒንግን ከኔትዎርክ አስተዳደር ጋር በማዋሃድ የሃብት አጠቃቀምን ለማሻሻል፣ የአገልግሎት ጥራትን ለመጨመር እና ችግሮች ከመከሰታቸው በፊት አስቀድሞ ለመተንበይ ያስችላቸዋልም ነው የተባለው።
ይህም የኔትዎርክ መጨናነቅን በመቅረፍ እና የዳታ ፍጥነትን በመጨመር እንዲሁም የኃይል ፍጆታን በመቀነስ ረገድ ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው ተገልጿል።
እንደ ኤሪክሰን ያሉ ዓለም አቀፍ እና ቴክኖሎጂውን በተግባር ያዋሉ ኩባንያዎች ሕብረት አባላት ለዚህ ቴክኖሎጂ እድገት በቢሊየን የሚቆጠር ዶላር ወጪ እያደረጉ መሆናቸውም ተመላክቷል።
ቴክኖሎጂው የአፍሪካ የቴሌኮም አውታረ መረቦች ይበልጥ ፈጣን፣ አስተማማኝ እና የደንበኞችን ፍላጎት ያማከሉ እንዲሆኑ የሚያደርጋቸው ሲሆን÷ በዚህም የአህጉሪቱን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን የሚያፋጥን ቁልፍ መሳሪያ ተደርጎ እንደሚወሰድ ኤ አይ አፍሪካ ዘግቧል።