Fana: At a Speed of Life!

ዲጂታል ግብርና ለዘርፉ ምርታማነት…

አዲስ አበባ፣ ጥር 6፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ዲጂታል ግብርና የዘርፉን ምርታማነትን በማሳደግ ለኢኮኖሚያዊ ዕድገት ትልቅ አስተዋጽኦ አለው አሉ የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ማንደፍሮ ንጉሴ (ዶ/ር)።

ዋና ዳይሬክተሩ ለግብርናው ዘርፍ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ፣ ዲጂታል ፈጠራ እና ዳታ ላይ የተመሰረቱ መፍትሔዎች አጠቃቀምን ለማሳደግ ከኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ጋር ስምምነት መደረሱን ተናግረዋል።

ግብርናን በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ማገዝ የአርሶና አርብቶ አደሮችን ምርታማነት በማሳደግ ህይወታቸውን እንደሚቀይር እና ለሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት ትልቅ ድርሻ እንዳለው አንስተዋል።

ከዲጂታላይዜሽን ጎን ለጎን ፈጠራን በዘርፉ ለማስኬድ እየተሰራ መሆኑን በማንሳት÷ በግብርና ፈጠራ ላይ ለተሰማሩ ወጣቶች ውድድር በማካሄድ ለአሸናፊዎች ፈጠራዎቻቸውን ወደ መሬት እንዲያወርዱ ለማስቻል እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

ለዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 መሳካትም የዲጂታል ግብርና ፕሮግራም የራሱ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አመልክተዋል።

በኢንስቲትዩቱ የዲጂታል ኢኖቬሽን ዳይሬክተር ግሩም ከተማ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ የግብርና መረጃዎችን ለመሰብሰብ እና የተሟላ መረጃን ለማግኘት አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ጥቅም ላይ ይውላል ብለዋል።

የአርሶና የአርብቶ አደሮችን ሙሉ መረጃዎች በመሰብሰብ ፍኖተ ካርታ በማዘጋጀት በዲጂታላይዜሽን ውስጥ እንዲካተቱ እየተሰራ መሆኑን ገልጸው÷ በዚህም በፋይዳ መታወቂያ አማካኝነት በልዩ መለያ የ57 ሺህ አርሶ አደሮችን መረጃዎች መሰብሰብ እንደተቻለ ጠቁመዋል።

የተለያዩ ተፈጥሯዊ አደጋዎች በሚከሰቱበት ጊዜም ለአርሶ አደሩ ማሳወቅ የሚያስችል የዲጂታል ስርዓት መዘርጋቱን አንስተው÷ በ “8028” እና “6777” ነጻ የስልክ መስመሮች አርሶ አደሮች የግብርና መረጃዎችንና የገበያ ዋጋን በሚፈልጉት ቋንቋ ማግኘት እንዲችሉ ተደርጓልም ነው ያሉት።

በሶስና አለማየሁ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.