የሻቢያ መንግሥት የሀገሪቱን ሰላም ለማደፍረስ በፋኖ ስም የሚነግዱ ሽፍቶችን ለማስታጠቅ በስውር የላከው ከ56 ሺህ በላይ የጦር መሣሪያ ጥይቶች ተያዙ
አዲስ አበባ፣ ጥር 6፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት የሻቢያ መንግስት ከኢትዮጵያ የውስጥ ባንዳዎች እና ታሪካዊ ጠላቶች ጋር በማበር የሀገሪቱን ሰላም ለማደፍረስ በፋኖ ስም የሚነግዱ ሽፍቶችን ለማስታጠቅ በስውር የላከውን ከ56 ሺህ በላይ የተለያዩ የጦር መሣሪያ ጥይቶችን ከሁለት ተጠርጣሪዎች ጋር በወልዲያ የፍተሻ ጣቢያ በቁጥጥር ሥር አውሏል፡፡
እጅ ከፍንጅ በቁጥጥር ሥር በዋሉት ሁለት ተጠርጣሪዎች ላይ በተደረገው የመጀመሪያ ደረጃ ምርመራ ጥይቶቹ በሻቢያ መንግስት እንደተላኩና ጽንፈኛው ሕወሓት በትግራይ ክልል መቐሌ ላይ ተቀብሎ ወደ አማራ ክልል ሸዋሮቢት በማስገባት በፋኖ ስም ለሚነግዱ ሽፍቶችን ለማድረስ ሲንቀሳቀሱ እንደነበር ተረጋግጧል።
ለሻቢያ መንግስት ድልድይ ሆኖ እየሠራ ያለው ፅንፈኛው የሕወሓት ቡድን ፅንፈኛው ፋኖን በማስታጠቅ የሀገራችንን ሰላም ለማደፍረስ አቅዶ ከኤርትራ በመቐሌ በኩል በስውር የላከውን 41 ሺህ 999 የክላሽ ጥይት፣ 14 ሺህ የብሬን ጥይት እና 800 የድሽቃ ጥይት በአጠቃላይ 56 ሺህ 799 ጥይቶች በሰሌዳ ቁጥር ኮድ 3 አ.አ B94744 የጭነት አይሱዙ ተሽከርካሪ ከሲሚንቶና ከብሎኬት ጋር አመሳስሎ በመጫን በአማራ ክልል ወልዲያ ከተማ አድርገው ወደ ሸዋሮቢት ለማስገባት ሲያጓጉዙ በወልዲያ የፍተሻ ጣቢያ ላይ በቁጥጥር ስር ውሏል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት ባደረገው ጠንካራ ክትትልና ፍተሻ ነው ጥር 5 ቀን 2018 ዓ.ም ከሁለት ተጠርጣሪዎች ጋር በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ እየተጣራባቸው የሚገኘው።
ባዳዎች እና ባንዳዎች ተቀናጅተው ሰላምና ደኅንነት ለማደፍረስና ሀገሪቱ እያካሄደች ያለችውን ልማትና ዕድገት ለማደናቀፍ በተለያዩ ጊዜ ሲንቀሳቀሱ በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ይታወቃል።
አሁን ላይም እነዚህ የጠላት ኃይሎች ሀገሪቱ ላይ አደጋ ለማድረስ እየተንቀሳቀሱ በመሆናቸው የፀጥታ ኃይሉ የጀመረውን ኦፕሬሽን አጠናከሮ እንደሚቀጥል በመግለጽ ሕብረተሰቡም ከፀጥታ ኃይሉ ጋር በመተባበር የተለመደውን ድጋፍ እንዲያደርግ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ጥሪ አቅርቧል።