Fana: At a Speed of Life!

ጥምቀትን በጎንደር ሐይማኖታዊ እሴቱን በጠበቀ መልኩ ለማክበር ዝግጅት ተጠናቅቋል – ብጹዕ አቡነ ዮሐንስ

አዲስ አበባ፣ ጥር 8፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የጥምቀት በዓልን በጎንደር ሐይማኖታዊ እሴቱን በጠበቀ መልኩ ለማክበር አስፈላጊው ዝግጅት ተጠናቅቋል አሉ የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ዮሐንስ።

ብጹዕ አቡነ ዮሐንስ በዓሉን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ፥ ጥምቀት ኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ልጆችን የእዳ ደብዳቤ ለመቅደድ በዮርዳኖስ የመጠመቁ መታሰቢያ በዓል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ኢየሱስ ክርስቶስ የተጠመቀው ለሰው ልጆች አርዓያ ለመሆን ነው፤ ስለሆነም የጥምቀት በዓልን ስናከበር በመተሳሰብና በአብሮነት ሊሆን ይገባል ብለዋል።

ኢየሱስ ክርስቶስ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ በመምጣት በዮሐንስ እጅ የተጠመቀው ሁሉም የሰው ልጆች እኩል መሆናቸውን ለማስተማር እንደሆነ አውስተዋል።

በዓሉን ስናከብር የተቸገሩትን በመርዳት፣ የተራቡትን በማብላት እና የታመሙትን በመጠየቅ ሊሆን ይገባል ነው ያሉት።

የጥምቀት በዓልን ለማክበር ወደ ጎንደር ለሚመጡ እንግዶች የከተማዋ ነዋሪዎች ኢትዮጵያዊ የእንግዳ ተቀባይነት ባህልን በሚያንጸባርቅ መልኩ እንዲቀበሉ ጠይቀዋል።

የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገራት እንግዶች የጥምቀት በዓልን በጎንደር እንዲያከብሩም ጥሪ አቅርበዋል።

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.