የገጠር ኮሪደር ስራ ፍሬ እያፈራ ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ጥር 9፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የተጀመረው የገጠር ኮሪደር ስራ ፍሬ እያፈራ ነው አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)።
በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት እና ተጠሪ ተቋማት የተሰሩትን የሞዴል ገጠር ኮሪደር ስፍራ በጎበኙበት ወቅት ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ይህንን ያሉት።
በከተማ የተጀመሩ የልማት ስራዎች ወደ ገጠሩም በማስፋፋት በሁሉም ክልሎች እና ዞኖች አዳዲስ የተሻገሩ የገጠር መንደሮች እየተሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በለምነቱና በሚያመርተው ልዩ ልዩ ምርቶች የሚታወቅ የጉራፈርዳ አካባቢው ነዋሪ የኑሮ ደረጃ በሚጠበቀው ልክ እንዳልሆነ በመግለጽ÷ ዛሬ የተመለከትነው የተሻገረ የገጠር ኮሪደር ስራ ተስፋ ሰጪ ነው ብለዋል።
ይህንን ጉዳይ በሀገር ደረጃ እንደየአካባቢው የተፈጥሮ ጸጋ መጠቀም ችለን የዜጎቻችንን ህይወት መቀየር ከቻልን የተሟላ ብልጽግና እናመጣለን ሲሉም ተናግረዋል።
በጉራፈርዳ የተሰራውን የገጠር ኮሪደር የራሱ መዋዕለ ሕጻናት መኖሩ ከሌሎቹ የተለየ እንደሚያደርገው አመላክተዋል።
በድምሩ ብልጽግናን እናረጋግጥ ሲባል በቁጥር የእያንዳንዱን ዜጋ ሕይወት መንካት አለበት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ በዚህም የማይቆም ቀጣይነት ያለውና ጥራት ያለው እድገት ማረጋገጥ እንደሚቻል አብራርተዋል።
በዚህ ሁሉ ሃብት ውስጥ ዜጎቻችንን አሁንም ማስተማር፣ የኑሮ ደረጃቸውን ማሻሻል፣ ቤታቸውን መቀየር ያስፈልጋልም ነው ያሉት።
እያንዳንዱ አርሶ አደር በአካባቢው ባለው ግብዓት የራሱን ቤት በመስራት ወደዚህ ደረጃ ማዘመን አለበት የሚል ሰርቶ ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
ይህንን ስራ ለመስራት ወጪው ዝቅተኛና የግንባታ ቁሳቁሶችም በአቅራቢያ የሚገኙ መሆናቸውን በመግለጽ÷ የጎደለው ሐሳብ ብቻ ነው ብለዋል።
የኮሪደር ስራውን አስፋፍቶ ማስቀጠል እንደሚገባ ገልጸው÷ ስራው ተሰርቶ እንዲጠናቀቅ ያስተባበሩ አመራሮችን እና ሰራተኞችን አመስግነዋል።
የተጀመረው የገጠር ኮሪደር ስራ ፍሬ እያፈራ እንደሆነና ጅማሮው ጥሩ እንደሆነ እንዲሁም ጠንክሮ በመስራትና በማባዛት የዜጎችን ሕይወት ለመቀየር መስራት እንደሚገባ አጽንዖት ሰጥተዋል።
በዮናስ ጌትነት