የኢትዮጵያን አስደናቂነት ለመገንዘብ ማድረግ የሚገባን ዐይናችንን መግለጥ ብቻ ነው – ሰላማዊት ካሳ
አዲስ አበባ፣ ጥር 10፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ የኢትዮጵያን አስደናቂነት ለመገንዘብ ማድረግ የሚገባን ዐይናችንን መግለጥ ብቻ ነው አሉ።
ሚኒስትሯ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ተፈጥሮ አድልታ ባስዋበችው ቤንች ሸኮ ዞን ተገንብቶ ዛሬ የተመረቀው ደንቢ ኢኮ ሎጅ ተፈጥሮን የሚወድ፣ የመንፈስ እርጋታን የሚሻ ሁሉ ሊያየው የሚገባ ድንቅ ስፍራ ነው ሲሉ ገልጸውታል።
የገበታ ለትውልድ አካል የሆነውና በመንግሥትና የግል አጋርነት በሚድሮክ ግሩፕ የተገነባው ኢኮ ሎጅ ልዩ የቱሪስት መስህብን መያዙን ተናግረዋል።
በኢኮ ሎጁ ዙሪያ ያሉት ግዙፉ የበበቃ የቡና እርሻ፣ ጥቅጥቅ ደን እና ሐይቅ ውብ የጎብኚዎች መዳረሻ እንደሚያደርገውም ገልጸዋል።
በቅርብ ርቀት ያለው የሚዛን አማን አውሮፕላን ማረፊያ ከየትኛውም ጫፍ የሚመጣን ጎብኚ በቀላሉ ወደ ደንቢ ኢኮ ሎጅ የሚያደርስ ስለመሆኑም አመላክተዋል።