ወራቤ ፓርክና የወንዝ ዳር ልማት..
አዲስ አበባ፣ ጥር 12፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በከተሞች ውስጥ የሚገኙ ፓርኮች አረንጓዴ ስፍራዎችና አደባባዮች የከተሞችን ውበት በማጉላት ከፍ ያለ አስተዋጽኦ ከማበርከታቸው ባሻገር ለነዋሪዎች መዝናኛና መናፈሻ በመሆን ዘርፈ ብዙ ማህበራዊ ፋይዳ አላቸው፡፡
ከዚህ እውነት በመነሳት በወራቤ ከተማ አስተዳደር ከ2016 ዓ.ም ጀምሮ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ስልጤ ዞን በግንባታ ላይ የሚገኘው የወራቤ ከተማ የመዝናኛ ፓርክ ፕሮጀክት በከተማዋ የዲጆ ወንዝ ዳርቻን አካቶ እየለማ ያለ ፓርክ ነው፡፡
የዞኑ ኮሙኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ ሱፊያን ሙስጠፋ ለፋና ዲጂታል እንደገለጹት፥ በአጠቃላይ 7 ሄክታር መሬት የሚሸፍነው የወራቤ መዝናኛ ፓርክ በኢትዮጵያ የፓርኮች ምደባ ስታንዳርድ መሰረት የክፍለ ከተማ ፓርክ ተብሎ የሚመደብ ነው።
በአጠቃላይ በአንድ ጊዜ እስከ 2ሺህ 500 ሰዎችን ለመዝናኛነት ማስተናገድ የሚችልበት አቅም እንዲኖረው ታቅዶ በመገንባት ላይ የሚገኝ ሲሆን፥ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከሚገኙ ትልልቅ ፓርኮች ውስጥ ምናልባትም ግንባር ቀደሙ ሊሆን የሚችል ነው፡፡
ከመልከዓ ምድራዊ አቀማመጥ አንጻር ለመዝናናትና ንጹህ የተፈጥሮ አየርን ለመተንፈስ በሚመች ማራኪ ስፍራ ላይ እየተገነባ የሚገኘው የወራቤ ፓርክ አካባቢውን ይበልጥ ወደ ደመቀ መስህብነት በመቀየር ላይ ነው፡፡
ፓርኩ በውስጡ የመሰብሰቢያ አዳራሽ፣ ካፌ፣ መዋኛ ገንዳ፣ የቅርጫት ኳስና የቴኒስ ኳስ ሜዳዎች፣ ዘመናዊ መጸዳጃና ገላ መታጠቢያ፣ አረንጓዴ ስፍራዎች፣ ፋውንቴንና ሌሎች ፕሮጀክቶችን አካትቶ እየተገነባ ይገኛል፡፡
ከእነዚህም ውስጥ አዳራሽ፣ ካፌ፣ ፋውንቴን፣ የቅርጫትና የቴኒስ ኳስ ሜዳ፣ የውስጥ ለውስጥ መንገድ፣ ውሃ መውረጃ ቦይ፣ ዘመናዊ መጻዳጃና የገላ መታጠቢያ እንዲሁም አርቴፊሻል ወንዝና ሌሎች አነስተኛ ግንባታዎች ተጠናቀዋል፡፡
ፓርኩ በከፊል አገልግሎት መስጠት በመጀመሩ ለከተማዋ ነዋሪዎችና ከተማዋን ለሚጎበኙ እንግዶች የእረፍትና የመዝናኛ ስፍራ ከመሆን ባሻገር ተከታታይ መንግስታዊና ህዝባዊ የስብስባ መድረኮችን እያስተናገደ ይገኛል፡፡
ከመዝናኛነት ባለፈ ህዝባዊ ሁነቶችን በፓርኩ ማስተናገድ የሚያስችሉ ሰፊ ስራዎች እየተሰሩ ሲሆን፥ ለህፃናት የእግር ኳስ፣ የቅርጫት ኳስ እና የእጅ ኳስ መጫወት የሚያስችሉ ደረጃቸውን የጠበቁ ሜዳዎች ተጠናቅቀው አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል።
የስልጤን ባህል በሚያሳይ መልኩ በዘመናዊ መንገድ የተገነባውና የካፍቴሪያ አገልግሎት የሚሰጠው ጎጆ ቤት በዙሪያው በተተከሉ የተለያዩ ተክሎች እንዲሁም በፋውንቴንና ወተርፎል ለተመልካች ሳቢ ሆኖ ይታያል፡፡
የህፃናት መጫወቻ፣ የሰርግ ፕሮግራምና ህዝባዊ ሁነቶችን የሚያስተናግዱ ቦታዎች፣ ሰውሰራሽ ወንዞች፣ ለዓሳ እርባታ የሚሆኑ ሀይቆችና አነስተኛ ኩሬዎች በፓርኩ ውስጥ እንደሚገኙ ኃላፊው አመልክተዋል፡፡
መዝናኛ ፓርኩ 75 በመቶ በጥላና በፍራፍሬ ዛፎች እንዲሁም ቀሪው በመንገድ የተሸፈነ ሲሆን፥ በ2018 በጀት ዓመት ብቻ 280 ለሚሆኑ ዜጎች የስራ ዕድል መፍጠር ችሏል።
በሁለት ምዕራፎች ከ120 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ በጀት ወደ ስራ የገባው ፕሮጀክቱ በምዕራፍ አንድ የግንባታ ሒደት ከ85 ሚለየን ብር በላይ ወጪ ተደርጎበታል።
በሁለተኛው የግንባታ ምዕራፍ ከ40 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ ልዩ ልዩ የውስጥ ግብዓቶች እየተሟሉ እንደሚገኙና ተጨማሪ ግንባታዎች እየተከናወኑ ይገኛል፡፡
የወራቤ መገለጫ በመሆን ከተማዋን አንድ እርምጃ ወደፊት የሚያራምድና የህዝቡን ባህላዊ እሴቶች የሚያስተዋውቅ እንደሚሆን የታመነበት ፓርኩ በቀጣይ ጊዜያት ለከተማ አስተዳደሩ የገቢ ምንጭ በመሆን ዘርፈ ብዙ ፋይዳ እንደሚሰጥ ይጠበቃል፡፡
በመዝናኛ ፓርኩ እየተከናወኑ ያሉ ቀሪ ስራዎች በፍጥነት እየተገባደዱ ሲሆን፥ በቀጣይ ጊዜያት ይዞታውንና አገልግሎቱን በማስፋት በሀገር ደረጃ ከሚታወቁ ግንባር ቀደም የከተማ ፓርኮች አንዱ ለማድረግ ግብ ተቀምጧል፡፡
ፓርኩ አሁን ባለበት የግንባታ ደረጃ በክልል ደረጃ የማረፊያና የመዝናኛ ቦታዎችን እጥረት የሚቀርፍና ዘርፈ ብዙ ፋይዳ መስጠት የሚችል መሆኑንም አቶ ሱፊያን አስረድተዋል፡፡