ኢትዮጵያ የተስፋ ብቻ ሳይሆን የሥራና የተጨባጭ ውጤት ምድር እየሆነች ነው – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ፣ ጥር 24፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ)ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ኢትዮጵያ ዛሬ የተስፋ ብቻ ሳይሆን የሥራና የተጨባጭ ውጤት ምድር እየሆነች ነው አሉ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከገበታ ለትውልድ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ የሆነውን የሸበሌ ሪዞርት በትናንትናው ዕለት መርቀው ለአገልግሎት ክፍት አድርገዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በማኅበራዊ የትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፥ ሪዞርቱ ኢትዮጵያን በአፍሪካ ቀዳሚ የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ ለተያዘው ጉዞ ትልቅ እጥፋት የሚፈጥር ነው ብለዋል፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ከሀሳብ ዘር እስከሚታይ ውጤት በሚመነዘሩ የትጋት ልኬቶች የተጀመሩት የገበታ ፕሮጀክቶች የሀገራችንን እምቅ ፀጋዎች ለዓለም ገበያ እያወጡ ይገኛሉ ነው ያሉት።
በመደመር እሳቤ እየተገነቡ የሚገኙት እነዚህ ፕሮጀክቶች ያለንን አቅም በማቀናጀት ለላቀ ውጤትና ከፍታ እንድንጓዝ የሚያግዙ ናቸው ብለዋል።
የሸበሌ ሪዞርት የሶማሌ ክልልን የሀገራዊ ልማት ትሩፋቶች ተጠቃሚ ከማድረግ ባሻገር የምስራቅ ኢትዮጵያን የቱሪዝም ዘርፍ ወደ አዲስ ምዕራፍ የሚያሸጋግር ትልቅ አቅም መሆኑን አንስተዋል፡፡