Fana: At a Speed of Life!

በክልሉ ምርታማነትን ይበልጥ ለማሳደግ ሕዝባዊ ንቅናቄ በመፍጠር ርብርብ ማድረግ ያስፈልጋል – አቶ አረጋ ከበደ

አዲስ አበባ፣ ጥር 24፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአማራ ክልል በሁሉም ዘርፍ ምርታማነትን በማሳደግ የተገኙ ውጤቶችን አጠናክሮ ለማስቀጠል አመራሩ ሕዝባዊ ንቅናቄ በመፍጠር ርብርብ ማድረግ ይጠበቅበታል አሉ የክልሉ ርዕሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ።

የክልሉ የ2018 በጀት ዓመት የስድስት ወራት የፓርቲና የመንግሥት ሥራዎች ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ በባሕር ዳር ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።

ርዕሰ መሥተዳድሩ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ በክልሉ ባለፉት ስድስት ወራት በሁሉም ዘርፍ ምርታማነትን በማሳደግ የሕዝቡን ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡

ለዚህም በክልሉ የ25 ዓመት አሻጋሪና ዘላቂ የልማት ዕቅድና የአምስት ዓመት ስትራቴጂያዊ ዕቅድ በተሻለ ሁኔታ እየተተገበረ መሆኑን አንስተዋል።

ለአብነትም በሰብል ልማት፣ በእንስሳት፣ በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና መሰል ሥራዎች ሞዴል የሆኑና ይበልጥ ሊሰፉ የሚችሉ ውጤቶችን ማስመዝገብ ተችሏል ነው ያሉት።

በአምራች ዘርፉ፣ በማዕድን፣ በቱሪዝም፣ የአገልግሎት አሰጣጥን በማሻሻልና በሌሎች ዘርፎች የተሻለ ዕድገት ማስመዝገብ ተችሏል ብለዋል፡፡

ችግሮችን በመቋቋም የተገኙ ውጤቶች የሚበረታቱ ናቸው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ አሁንም የክልሉን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ዘላቂነት ማረጋገጥ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።

የሕዝብን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት በማሳደግ የተገኙ ውጤቶችን ማስፋት እንደሚገባ ጠቁመው፥ ለዚህም አመራሩ በሁሉም ዘርፍ ምርታማነትን ለማሳደግ ሕዝቡን በነቂስ በማሳተፍ በጋራ መረባረብ እንደሚጠበቅበት አስገንዝበዋል።

በበጀት ዓመቱ ቀሪ ወራት በየዘርፎቹ የተቀመጡ ግቦች እንዲሳኩ በተለይም በሥራ ዕድል ፈጠራ፣ የኑሮ ውድነትን በመቅረፍና የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ የተለየ ትኩረት ተሰጥቶ መሥራት እንደሚገባ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.