Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ በእኩል አጋርነት ለመተሳሰርና ለመልማት ዝግጁ ናት – ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ

አዲስ አበባ፣ ጥር 26፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ ኢትዮጵያ በእኩል አጋርነት ከዓለም ጋር ለመተሳሰርና ለመልማት ዝግጁ ናት አሉ።

በየዓመቱ በተባበሩት አረብ ኤሚሬትስ ዱባይ የሚዘጋጀው የዓለም መንግስታት የምክክር ጉባዔ እየተካሄደ ይገኛል፡፡

ፕሬዚዳንት ታዬ በጉባኤው ላይ ባደረጉት ንግግር፥ ኢትዮጵያ የአፍሪካን የኢንዱስትሪ ሽግግር የሚደግፉ ስትራቴጂያዊ ተግባራትን በማከናወን ላይ እንደምትገኝ አንስተዋል።

ለአብነትም ሙሉ በሙሉ በራስ አቅም የተገነባው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ጠቅሰው፥ ግድቡ ከ6 ሺህ ሜጋ ዋት በላይ ኃይል ማመንጨት እንደሚችል ተናግረዋል።

በተጨማሪም በምግብ ራስን ለመቻል ከስንዴ አስመጪነት በአፍሪካ ትልቁ የስንዴ አምራች ወደመሆን መሸጋገሯን ያነሱት ፕሬዚዳንቱ፥ ባለፈው አመት 640 ሺህ ሜትሪክ ቶን ቡና ማምረቷን ጠቅሰዋል።

በዓመት 110 ሚሊየን መንገደኞችንና 3 ሚሊየን ቶን ጭነት የማስተናገድ አቅም ያለውን የቢሾፍቱ ዓለምአቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ በ12 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር መጀመሩን ጠቅሰው፥ ይህም የአፍሪካን የኢንዱስትሪ ሽግግር ከሚደግፉ ተግባራት አንዱ ነው ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ የፋይናንስ ተቋማትን በማጠናከር እንዲሁም የመንግስትና የግሉን ዘርፍ ትብብር በማሳደግ ስራ ፈጣሪዎችንና የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ይበልጥ እንደምታበረታታ አጽንኦት ሰጥተዋል።

ፕሬዚዳንት ታዬ አክለውም አፍሪካ በፍጥነት እየተለወጠ በሚገኘው ዓለም ውስጥ እንደ ተመልካች ሳይሆን እንደ ንቁ መሐንዲስ መታየት አለባት ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ ብሎም አፍሪካ በእኩል አጋርነት ለመተሳሰር፣ ለመልማትና ለመሳተፍ ዝግጁ መሆናቸውንም ፕሬዚዳንቱ አረጋግጠዋል፡፡

ከዓለም ለውጥ ጋር ተያይዞ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች፣ ታዳሽ ኃይል፣ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂና ዲጂታል ፋይናንስ የአፍሪካን ልማት ለማፋጠንና የረዥም ጊዜ መዋቅራዊ እንቅፋቶችን ለመሻገር መልካም እድሎች ናቸው ብለዋል።

12 በመቶ የሚሆነውን የዓለም ንግድ የሚያስተናግደው የቀይ ባህር ስትራቴጂያዊ ጠቀሜታ ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው፥ ከጠባብ ቀጣናዊ አስተሳሰብ በመውጣት ዓለምአቀፍ የትብብር ማዕቀፍ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።

እኛ አፍሪካውያን በጋራ የጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ ትብብር በመገንባት አቋማችንን ማስታረቅ ይገባናል ሲሉም አሳስበዋል።

እውነተኛ ዓለምአቀፍ አጋርነት ሊኖር እንደሚገባ ጠቁመው፥ ኢትዮጵያ በዓለምአቀፉ ለውጥ ላይ አስተዋጽኦ ለማድረግ ቁርጠኛ እንደሆነች ተናግረዋል።

በሶስና አለማየሁ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.