Fana: At a Speed of Life!

የሞባይል ገንዘብ ዝውውር አገልግሎት ተጠቃሚዎች ቁጥር 58 ሚሊየን ደርሷል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ጥር 26፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያ የሞባይል ገንዘብ ዝውውር አገልግሎት ተጠቃሚዎች ቁጥር 58 ሚሊየን ደርሷል አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ከምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች እንዲሁም በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ስድስት ወራት አፈጻጸም ዙሪያ ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በዚህም በዲጂታል አገልግሎት በተለይም በሞባይል አገልግሎት ከፍተኛ እድገት መመዝገቡን አንስተዋል።

ከለውጡ በፊት የሞባይል ስልክ ተጠቃሚዎች ቁጥር 37 ሚሊየን እንደነበር አስታውሰው፤ በአሁኑ ወቅት ኢትዮ ቴሌኮም ብቻ 87 ሚሊየን ደንበኞች ማፍራቱን ተናግረዋል።

ሳፋሪኮም ከ10 ሚሊየን በላይ ደንበኞች አሉት ብለዋል።

ከለውጡ ወዲህ የሞባይል ተጠቃሚው ቁጥር በ60 ሚሊየን መጨመሩን ገልጸው፤ በአሁኑ ወቅት ከ97 ሚሊየን በላይ ሰዎች የሞባይል ተጠቃሚ መሆናቸውን አብራርተዋል።

5ጂ ኔትዎርክ 28 ከተሞች ገብቶላቸዋል በቅርቡ 30 ከተሞች ይደርሳቸዋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ 1 ሺህ 70 ከተሞች የ4ጂ ኔትዎርክ እንደገባላቸው ጠቅሰዋል።

በፋይናንስ ዘርፍ ሶስት ዓመት የሆነው የሞባይል ገንዘብ ዝውውር አገልግሎት አሁን ላይ 58 ሚሊየን ኢትዮጵያውያን የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ባለፉት ሶስት ዓመታት በተሰራው ስራ በሞባይል የሚደረገው የገንዘብ ዝውውር በጥሬ ገንዘብ ከሚደረገው በልጧል፤ ይህም የፖሊሲ ለውጥ ውጤት ነው በማለት ገልጸዋል።

በሶስና አለማየሁ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.