የጉራግኛ የፊደል ገበታ በ2013 ዓ.ም በተመረጡ ትምህርት ቤቶች የቅድመ መደበኛ ተማሪዎችን ለማስተማር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ተገለፀ
አዲስ አበባ ፣ ነሃሴ 17፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የጉራጊኛ የፊደል ገበታ በ 2013 ዓ.ም በሁሉም ወረዳዎች በተመረጡ ትምህርት ቤቶች የቅድመ መደበኛ ተማሪዎችን ለማስተማር ዝግጅት እየተደረገ እንደሆነ ተገለጸ።
የፊደል ገበታዉ ለሙከራ የቅድመ መደበኛ ተማሪዎች የሚማሩ ሲሆን ይህንንም የሚያስተምሩ መምህራኖች ስልጠና እንደሚሰጥ ተነግሯል።
መምህራኖች ስልጠናውን ከወሰዱ በኋላ ህጻናትን መሰረት ማስያዝ እንዳለባቸዉም የገለፁት በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የስነ ልሳንና ስነ ተግባቦት መምህር ዶክተር ፈቀደ ምኑታ በሚቀጥለዉ አመት ለ1ኛ ክፍል ለማስተማር ግብአት የማዘጋጀት ስራም እንደሚሰራ አብራርተዋል።
በተመሳሳይ የጉራጌ ዞን ባህል ቱሪዝም ስፖርት መምሪያ የቋንቋና ስነ ጥበብ ቡድን መሪ አቶ ባህሩ ሊላጋ የጉራግኛ ፊደል ገበታ ማስተማር በቀጣዩ ዓመት እንደሚጀመር አረጋግጠዋል።
የጉራግኛ ቋንቋ ለማልማት ተነሳሽነት የሚያስፈልገዉ እንደሆነና የሙያ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ የተናገሩት ዶክተር ፈቀደ ምሁራኖች በእዉቀት ማገዝ እንዳለባቸዉም መግለፃቸውን የጉራጌ ዞን መንግስት ኮሚኒኬሽን መረጃ ያመለክታል።
ለሙከራ የሚሆኑ ከሁሉም ወረዳዎች ሁለት ሁለት ትምህርት ቤቶች በመምረጥ የቅድመ መደበኛ ተማሪዎች ፊደሉን እንዲያዉቁት የማስተማር ስራ እንደሚሰራም አብራርተዋል።
ለዚሁ የሚሆኑ ከየትምህርት ቤቶች ሁለት መምህራኖች እንዲሰለጥኑ ይደረጋል ያሉ ሲሆን የቴክኒክ ኮሚቴዉ በቀጣይ ለትምህርት በሚውለው ግብአት ላይ በተገቢዉ ዉይይት እንዳደረገም ተጠቁሟል።