Fana: At a Speed of Life!

አፍሪካ የኢኮኖሚ ችግሮችን ለመፍታት አኅጉራዊ የፋይናንስ ተቋም ያስፈልጋታል – ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ የካቲት 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአፍሪካ ሀገራት የሚጋሩትን የኢኮኖሚና የፋይናንስ ችግር ለመፍታት አኅጉራዊ የፋይናንስ ተቋም መመስረት ያስፈልጋል አሉ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር)፡፡

በሳዑዲ አረቢያ እና በዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) ትብብር የተዘጋጀውና በፍጥነት በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት ኢኮኖሚ ላይ ያተኮረው ጉባኤ እየተካሄደ ነው።

ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) በጉባኤው የሁለተኛ ቀን መድረክ ላይ እንዳሉት፥ ዓለምአቀፍ የፋይናንስ ተቋማት በተለይም ለአፍሪካ ሀገራት የሚያቀርቡት ድጋፍ ከፍተኛ ውስንነት አለበት፡፡

በአሁኑ ወቅት በርካታ ሀገራት በማዕከላዊ ባንኮቻቸው የመጠባበቂያ ክምችትና በዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) ድጋፍ ላይ ጥገኛ ለመሆን እየተገደዱ ይገኛሉ ነው ያሉት፡፡

የአፍሪካ ሀገራት በኢኮኖሚና ፋይናንስ ዘርፉ የሚያጋጥማቸውን የጋራ ችግር ለመፍታት አኅጉራዊ የፋይናንስ ተቋም ማቋቋም እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል፡፡

ይህም እየተዳከመ ለሚገኘው ዓለምአቀፍ የፋይናንስ ድጋፍ ወሳኝ መፍትሔ እንደሚሆን ገልጸው፥ የሚቋቋመው ተቋም ከዓለምአቀፉ የፋይናንስ ስርዓት ማዕቀፍ ጋር የተጣጣመ ሊሆን እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡

የብሔራዊ ባንክ ገዥው በዚሁ ወቅት፥ ሀገራት የፋይናንስ ድጋፍ የሚያገኙት ባላቸው የኢኮኖሚ አቅም መሰረት መሆኑን ለሚያትተው የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም የኮታ ስርዓት ድጋፋቸውን ገልጸዋል፡፡

ሆኖም ኢትዮጵያ በኢኮኖሚው ካስመዘገበቻቸው ውጤቶችና ተቋማዊ የማሻሻያ ስራዎች አንጻር አሁናዊ የፋይናንስ ድጋፍ ድርሻዋ ሊያድግ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

በውይይት መድረኩ ላይ የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) ማኔጂንግ ዳይሬክተር ክሪስታሊና ጆርጂዬቫ፣ የዓለም ባንክ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አና ቤርዴን ጨምሮ የተለያዩ ሀገራት የማዕከላዊ ባንክ ገዥዎች ተገኝተዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.