ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ከዛምቢያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ከዛምቢያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሙላምቦ ሃይምቤ ጋር ተወያይተዋል።
በውይይታቸውም በሁለቱ ሀገራት የጋራ ጥቅሞች ላይ የተመሰረቱ የሁለትዮሽና አኅጉራዊ ጉዳዮች ዙሪያ የመከሩ ሲሆን፥ ግንኙነታቸውን በተለያዩ ዘርፎች የበለጠ ለማጠናከር ተስማምተዋል፡፡
ጌዲዮን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት የኢትዮጵያ እና ዛምቢያ ግንኙነት ታሪካዊና ጠንካራ መሆኑን ገልጸው፥ የሀገራቱ የፖለቲካ ግንኙነት ወደ ኢኮኖሚ ትብብር መሸጋገር እንዳለበት አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ የንግድ ማኀበረሰብ የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ምርቶችን ወደ ዛምቢያ ገበያ የማቅረብ አቅም እንዳላቸውም አስረድተዋል።
የዛምቢያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሙላምቦ ሃይምቤ በበኩላቸው፥ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የንግድ ግንኙነት የበለጠ ማጠናከር እንደሚገባ ጠቅሰዋል።
ሚኒስትሩ በ48ኛው የአፍሪካ ኅብረት የሥራ አስፈጻሚዎች ስብሰባና በ39ኛው የመሪዎች ጉባዔ ላይ ለመሳተፍ አዲስ አበባ መግባታቸው የሚታወስ ነው።