ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን በአፍሪካ ሕብረት መሪዎችና ጣሊያን አፍሪካ ጉባዔዎች ላበረከተው አስተዋጽኦ እውቅና ተሰጠው
አዲስ አበባ፣ የካቲት 12፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን በአፍሪካ ሕብረት መሪዎችና በጣልያን አፍሪካ ጉባኤዎች ላይ ሰፊ የዘገባ ሽፋን በመስጠት ላበረከተው አስተዋጽኦ እውቅና ተሰጥቶታል።
በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስተባባሪነት የተዘጋጀውና የሁለቱ ጉባኤዎች በስኬት መጠናቀቅ አስተዋፅኦ ላበረከቱ አካላት እውቅና የመስጠት መርሐ ግብር ተካሂዷል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት ከጉባኤዎቹ በተጨማሪ የጎንዮሽ ውይይቶች መካሄዳቸውን ጠቅሰው÷ በስኬት መጠናቀቃቸው የሀገርን ጠንካራ አቋም የሚያሳይና ገፅታን የሚገነባ መሆኑን ተናግረዋል።
ጉባኤዎቹ የኢትዮጵያን የዲፕሎማሲ ማዕከልነት ያሳዩ መሆናቸውን ገልጸው÷ በቀጣይ የሚካሄዱ ትልልቅ ዓለም አቀፍ መድረኮችን በተሻለ አቅም ለማስተናገድ ዝግጁነትን ያሳድጋል ብለዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋዬ በበኩላቸው÷ ለጉባኤው መሳካት የደከሙ ሁሉ የሀገርን ገፅታ አስተዋውቀዋል በማለት ምስጋና አቅርበዋል።
በመድረኩ የፌደራል ፖሊስ፣ የብሔራዊ ደሕንነት ተቋማት፣ የጤናና የትራንስፖርት ዘርፎች እንዲሁም ሚዲያ ተቋማት በቅንጅት በመስራታቸው ጉባኤዎቹ በስኬት መጠናቀቃቸው ተመላክቷል።
በማህሌት ካሳሁን