Fana: At a Speed of Life!

ምርጫ የመምረጥና የመመረጥ መብት

በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 38(1) መሠረት ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ በቀለም፣ በዘር፣ በብሔር፣ በብሔረሰብ፣ በፆታ፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖት፣ በፖለቲካ ወይም በሌላ አመለካከት ወይም በሌላ አቋም ላይ የተመሰረተ ልዩነት ሳይደረግበት፡-

• በቀጥታ እና በነጻነት በመረጣቸው ተወካዮች አማካኝነት በሕዝብ ጉዳይ አስተዳደር የመሳተፍ፣

• እድሜው 18 አመት ሲሞላው/ት በሕግ መሰረት የመምረጥ፣

• በማናቸውም የመንግስት ደረጃ በየጊዜው በሚካሄድ ምርጫ የመምረጥና የመመረጥ መብት አለው።

ምርጫው ሁሉ አቀፍ፣ በሁሉም እኩልነት ላይ የተመሰረተ እና በምስጢር ድምጽ አሰጣጥ መራጩ ፍቃዱን በነጻነት የሚገልጽበት ዋስትና የሚሰጥ መሆን እንዳለበት ተቀምጧል።

ከዚህ አንፃር በምርጫ የፖለቲካ ታርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011 እንዲሁም በአዋጅ ቁጥር 1394/2017 እንደተሻሻለው በዝርዝር የተቀመጡ መስፈርቶች አሉ፡፡

ሀ. የመምረጥ መብት

በሀገራችን ሕገ-መንግሥት የመምረጥ መብት የኢትዮጵያዊ ዜግነት ላለው ብቻ የተሰጠ መብት በመሆኑ በዜግነት ኢትዮጵያዊ ያልሆነ ሰው በመራጭነት የመሳተፍ መብት የለውም።

ከዚህ በተጨማሪ በመራጭነት ለመሳተፍ አስቀድሞ መሟላት ያለባቸው ቅድመ ሁኔታዎች ያሉ ሲሆን አነዚህ ቅድመ ሁኔታዎችም በአዋጅ ቁጥር 1162/2011 አንቀጽ 18፣ በአዋጅ ቁጥር 1394/2017 እንደተሻሻለው ተመላክተዋል።
በዚህ መሰረትም ማንኛውም፡-

• ኢትዮጵያዊ ዜጋ ከሆነ፣

• በድምጽ መስጫው ዕለት ዕድሜው 18 (አስራ ስምንት) አመትና ከዚያ በላይ ከሆነ፣

• በአንድ የምርጫ ክልል ቢያንስ ለስድስት ወር የኖረ ከሆነ በመራጭነት የመሳተፍ መብት አለው፡፡

ሆኖም በአዕምሮ ህመም ምክንያት የመወሰን አቅም የሌለው መሆኑ ስልጣን ባለው አካል ወይም በበቂ ማስረጃ የተረጋገጠበት ሰውና የመምረጥ መብቱ በሕግ ወይም አግባብ ባለው ሕግ መሠረት በፍርድ ቤት ውሳኔ የተገደበበት ሰው በመራጭነት ተመዝግቦ በምርጫ የመሳተፍ መብት የሌለው መሆኑን ከአዋጁ አንቀጽ 18(3) መረዳት ይቻላል፡፡

እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባው የመምረጥ መብቱ የተረጋገጠለት ማንኛውም ሰው እስቀድሞ የመራጭነት ካርድ በእጁ ማድረግ የሚጠበቅበት ሲሆን በምርጫ ቀንም በምርጫ ጣቢያ ቀርቦ የፈለገውን ተመራጭ የመምረጥ መብት እንዳለው በሕገ-መንግሥቱም ሆነ በአዋጁ ላይ ተቀምጧል።

ለ. የመመረጥ መብት

በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ-መንግስት መሰረት የመመረጥ መብት የኢትዮጵያዊ ዜግነት ላለው ብቻ የተሰጠ መብት በመሆኑ በዜግነት ኢትዮጵያዊ ያልሆነ ሰው በተመራጭነት የመሳተፍ መብት የለውም።

በኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ-ምግባር አዋጅ አንቀጽ 31 በአዋጅ ቁጥር 1394/2017 እንደተሻሻለው መሠረት ለተመራጭነት በእጩነት ለመመዝገብ የፈለገ ማንኛውም ሰው፡-

• ኢትዮጵያዊ ዜጋ መሆን፣

• በድምጽ መስጫው ዕለት እድሜው 21 ዓመት ወይም ከዚያ በላይ መሆን፣

• ከምርጫው ዕለት አስቀድሞ በምርጫ ክልሉ ውስጥ በመደበኛነት አንድ ዓመት ከኖረ ወይም የትውልድ ቦታው በእጩነት ሊቀርብበት በፈለገበት የምርጫ ክልል ውስጥ መሆን፣

• በሕግ ወይም በፍርድ ቤት ውሳኔ የመመረጥ ወይም የመምረጥ መብቱ ያልተገፈፈ መሆን፣

• በአዕምሮ ህመም ምክንያት ለመወሰን ብቃት የሌለው መሆኑ ስልጣን ባለው አካል ወይም በበቂ ማስረጃ ያልተረጋገጠበት መሆን ይጠበቅበታል፡፡

ከላይ ከተዘረዘሩ መመዘኛዎች በተጨማሪ በግል የቀረበ እጩ ማለትም የግል ተመራጭ በአካባቢው መስተዳድር የተረጋገጠ እድሜያቸው 18 ዓመትና ከዚያ በላይ ከሆናቸው እና የመምረጥ መብታቸው በሕግ፣ በፍርድ ቤት ውሳኔ ወይም በአዕምሮ ህመም ምክንያት ያልተገደበ የምርጫ ክልሉ ነዋሪዎች ውስጥ ከአምስት ሺህ የማያንስ የድጋፍ ፊርማ ማቅረብ እንዳለበት በአዋጁ ላይ በአስገዳጅነት ተደንግጓል።

በልዩ ሁኔታ የግል እጩ ተወዳዳሪው የአካል ጉዳተኛ ከሆነ ማቅረብ ያለበት የድጋፍ ፊርማ ብዛት ከሶስት ሺህ የማያንስ መሆን እንዳለበት ተመላክቷል።

የምርጫ መርሆዎች:-
ምርጫ ሊያሟላቸው የሚገቡ መርሆዎች በአዋጁ አንቀጽ 5 ተዘርዝረዋል፡፡ ይኸውም፡-

• ማንኛውም ምርጫ ሁሉን አቀፍ፣ ቀጥተኛ፣ በምስጢር ድምፅ አሰጣጥ መራጩ ፈቃዱን በነፃነት የሚገልጽበት እና ያለ ምንም ልዩነት በሚደረግ ህዝባዊ ተሳትፎ ላይ የተመሰረተ መሆን፣

• የመምረጥ ወይም የመመረጥ መብቱ በህግ ወይም በፍርድ ቤት ውሳኔ ያልተገደበ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ መምረጥ ወይም መመረጥ መብቱ የተጠበቀ መሆን እና ለመምረጥም ሆነ ለመመረጥ ያለመገደድ፣

• የእያንዳንዱ መራጭ ድምፅ እኩል መሆን፣

• እያንዳንዱ መራጭ ድምጽ መስጠት የሚችለው በአካል በመገኘት መሆን ናቸው፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.