ፋና መድረክ ለሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች እድል የሚሰጥ ነው – ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች
አዲስ አበባ፣ የካቲት 19፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ፋና መድረክ በመርህ የሚዘጋጅና ለሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች እድል የሚሰጥ ነው አሉ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች፡፡
ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ በማስመልከት ባዘጋጀው ፋና መድረክ የክርክር መርሐ ግብር ላይ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡
ፋና መድረክ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች የፖሊሲ አማራጭ በጥልቅ የሚሞገትበት፣ ፓርቲዎች በሰለጠነ የውይይት ምህዳር እርስ በእርስ የሚጠያየቁበትና አማራጫቸውን ለህዝብ ያለገደብ የሚያሻግሩበት መርሐ ግብር ነው፡፡
በዚህም መሰረት የትምህርት ፖሊሲን አስመልክቶ በተካሄደው የክርክር መድረክ ላይ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)፣ ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት፣ ብልፅግና እና ኅብር ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ተሳታፊ ሆነዋል፡፡
የመድረኩ ተሳታፊ ፓርቲዎች ፋና መድረክ ፖሊሲዎች በሀሳብ እንዲጠሩና ህብረተሰቡ የፖሊሲ አማራጮችን እንዲመዝን እያስቻለ መሆኑን ገልጸው፥ ይህም በምርጫ ወቅት ድምጹን በጥሩ ግንዛቤ እንዲሰጥ ያስችለዋል ነው ያሉት፡፡
መድረኩ በመርህ የሚዘጋጅና ለሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች እድል የሚሰጥ መሆኑን ፓርቲዎቹ ገልጸዋል፡፡
ፋና መድረክ ዘወትር ቅዳሜ ምሽት በፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን በሬድዮ፣ ቴሌቪዥንና በዲጂታል አማራጮች ለአድማጭ ተመልካቾች ይቀርባል።
በአፈወርቅ እያዩ