Fana: At a Speed of Life!

ከሻይ ቅጠል ልማት የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ ነው – ባለስልጣኑ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 19፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ከሻይ ቅጠል ልማት የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ ነው አሉ የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ (ዶ/ር)፡፡

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን፣ የግብርና ሚኒስቴርና የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ አመራሮችና ባለሙያዎች በጅማ ዞን ሸቤ ሶንቦና ሰቃ ጮቆርሳ ወረዳዎች የሻይ ቅጠል ልማት የመስክ ምልከታ አድርገዋል።

ዋና ዳይሬክተሩ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ ከ2015 ዓ.ም ወዲህ የሻይ ቅጠል ልማትን ለማስፋፋት ውጤታማ ስራዎች ተከናውነዋል፡፡

ኢትዮጵያ ለሻይ ቅጠል ልማት ምቹ ስነምህዳር ቢኖራትም ዘርፉ ትኩረት ተነፍጎት መቆየቱን አስረድተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከሻይ ቅጠል ልማት የምታገኘውን ገቢ ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፥ ከ3 አመት በኋላ ከዘርፉ 700 ሚሊየን ዶላር ገቢ ይገኛል ነው ያሉት፡፡

የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌቱ ገመቹ በበኩላቸው፥ በክልሉ በ5 አመት ውስጥ 30 ሺህ ሄክታር መሬት በሻይ ቅጠል ተክሎች ለመሸፈን ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህ አመት 3 ሺህ ሄክታር መሬት በሻይ ቅጠል ለማልማት እየተሰራ ሲሆን፥ 400 ሚሊየን ችግኞች እየተዘጋጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በሙክታር ጠሃ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.