ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በአዘርባጃን ያደረጓቸው ጉብኝቶች የሀገራቱን ትብብር ያጠናክራሉ – የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት
አዲስ አበባ፣ የካቲት 20፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአዘርባጃን የተለያዩ ተቋማት ያደረጓቸው ጉብኝቶች የሀገራቱን ትብብር ይበልጥ የሚያጠናክሩ ናቸው አለ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት፡፡
በአዘርባጃን ይፋዊ ጉብኝት እያደረጉ የሚገኙት ጠቅላይ ሚኒስትሩና ልዑካቸው የሀገሪቱን የሕዝብ አገልግሎትና ማኅበራዊ ፈጠራ የመንግሥት ኤጀንሲ የፈጠራ ማዕከል ጎብኝተዋል፡፡
ጉብኝቱ አዘርባጃን በሰው ሰራሽ አስተውሎት የሚመራ አስተዳደርን ለማስፋፋትና የሕዝብ አገልግሎቶችን በዲጂታል ለማዘመን የምትከተለውን ስትራቴጂያዊ አካሄድ የሚያሳይ መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ገልጿል፡፡
በተጨማሪም የሀገሪቱ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ኢንጂነሪንግና የአመራር ሥልጠና ዋና ማዕከል የሆነውን የሰው ሰራሽ አስተውሎት አካዳሚ ተዘዋውረው ተመልክተዋል።
ልዑኩ ጉብኝቱን በመቀጠል በአካባቢው ካሉ ትላልቅ የነዳጅና የጋዝ ማቀነባበሪያ ማዕከላት አንዱ የሆነውን ሳንጋቻል ተርሚናልና አላት ነፃ የኢኮኖሚ ቀጣና መጎብኘቱም ተገልጿል፡፡
እነዚህ ጉብኝቶች በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የንግድ፣ የኢነርጂና የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ትብብር ይበልጥ የማጠናከር አቅም እንዳላቸውም ነው የተገለጸው፡፡