በኦሮሚያ ክልል የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ የአደጋ ስጋት ተጋላጭነት ቀንሷል
አዲስ አበባ፣ የካቲት 24፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኦሮሚያ ክልል ህብረተሰቡን ባሳተፈ መንገድ እየተከናወነ በሚገኘው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ የአደጋ ስጋት ተጋላጭነት ቀንሷል አለ የክልሉ ግብርና ቢሮ፡፡
የቢሮው ምክትል ኃላፊ ኤሊያስ ከድር ለፋና ዲጂታል እንደገለጹት፥ በክልሉ በዘንድሮ በጋ 3 ነጥብ 2 ሚሊየን ሄክታር መሬት ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ለማከናወን ታቅዶ ወደ ተግባር ተገብቷል።
የተራቆቱ መሬቶችን ከሰውና ከእንሰሳት ንክኪ ነጻ መደረጋቸውን ጠቅሰው፤ የአፈር መሸርሸርን ለመከላከል የእርከን ስራዎች በስፋት መሰራታቸውን ገልጸዋል።
ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ባቀናጀ መንገድ በስፋት እየተሰራ በሚገኘው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ደርቀው የነበሩ ሀይቆች ማገገማቸውና ተጋላጭነት መቀነሱን አብራርተዋል፡፡
በተጨማሪም የተተከሉ ችግኞችን የጽድቀት መጠን ከፍ ለማድረግ ችግኞችን የመንከባከብ ተግባር መከናወኑን ጠቅሰው፥ የአፈር እና ውሃ ጥበቃ ስራ በአጠቃላይ የግብርና ምርታማነት መጨመር ላይ አዎንታዊ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሆነ ጠቁመዋል።
የበጋ ወቅት የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ የተከናወነባቸውን አካባቢዎች ጨምሮ በክረምት ችግኝ ለመትከል 4 ነጥብ 95 ቢሊየን ችግኞች ለማዘጋጀት ታቅዶ እየተሰራ እንደሆነ አመልክተዋል።
የሚዘጋጁት ችግኞች ሀገር በቀልና ከአካባቢው አየር ንብረት ጋር የሚስማሙ መሆናቸውን ገልጸው፥ የመሬት ዝግጅቱ ተጠናክሮ መቀጠሉን አመልክተዋል፡፡
የእንስሳት መኖ፣ የፍራፍሬ፣ የቡና እና ለሌሎች አገልግሎቶች የሚውሉ እጽዋት ችግኞች ትኩረት ተሰጥቷል ብለዋል፡፡
በአቤል ንዋይ