ሁለንተናዊ የሀገር እድገትን ለማሳለጥ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሚና ሊጠናከር ይገባል – አቶ አደም ፋራህ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 26፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሀገር ግንባታን ለማፋጠን የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በንቃት ሊሳተፉ ይገባል አሉ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ም/ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ፡፡
5ኛው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሳምንት “ራስን መቻል ለዘላቂ ሰላምና ለአካታች ልማት” በሚል መሪ ሃሳብ እየተካሄደ ነው፡፡
አቶ አደም ፋራህ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ መንግሥት ለሀገር እድገትና ብልጽግና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሚና ትልቅ መሆኑን ይገነዘባል፡፡
በባለፉት የለውጥ ዓመታት መንግሥትና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በሀገራዊ ጉዳይ ላይ ተባብረው መስራት እንዲችሉ የቅንጅትና ትብብር ማዕቀፍ መዘጋጀቱን አስታውሰዋል፡፡
ክልሎችን ጨምሮ የሕግ ማሻሻያ እና ትግበራ መደረጉን ገልጸው÷ ይህም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን ዘመናዊ፣ ውጤታማ እና ቀልጣፋ አድርጓል ነው ያሉት፡፡
ባለፉት ዓመታት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ቁጥር በሶስት እጥፍ ማደጉን ጠቁመው÷ በአሁኑ ጊዜ 8 ሺህ 410 መድረሱን ገልጸዋል፡፡
የሀገር ግንባታ እና የብልጽግና ጉዞን ለማፋጠን የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በሀገራዊ ምክክር፣ በሽግግር ፍትሕ፣ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫና በባሕር በር ጥያቄ በንቃት እንዲሳተፉና የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
እስከ የካቲት 28 ቀን 2018 ዓ.ም በሚቆየው መርሐ ግብር ከ120 በላይ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ስራቸውን በኤግዚቢሽን ማዕከል ማስተዋወቅ ጀምረዋል፡፡
በምንተስኖት ሙሉጌታ
👉ለፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎች የፋና ዲጂታል አድራሻዎችን ከአስተያየት መስጫ ሳጥን ያግኙ፡-