Fana: At a Speed of Life!

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል 891 ሺህ ቤተሰብ የጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚ ሆነዋል

አዲስ አበባ፣ የካቲት 28፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል 891 ሺህ ቤተሰብ የጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚ ሆነዋል አለ የክልሉ ጤና ቢሮ።

የጤና ቢሮ የ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ግማሽ አፈፃፀም ግምገማ በወልቂጤ ከተማ እያካሄደ ሲሆን÷ በሁሉም ዘርፎች በተከናወኑ ስራዎች አበረታች ውጤት መመዝገቡ ተመላክቷል።

የቢሮው ኃላፊ አቶ ሳሙኤል ዳርጌ በዚህ ወቅት÷ በሽታ መከላከልን በማጠናከር የጤና ተቋማት ግንባታ፣ አዲሱን የጤና ኤክስቴንሽን ፍኖተ ካርታና ጽዱ ኢትዮጵያን ተግባራዊ በማድረግ እንዲሁም የእናቶችን የወሊድ ማቆያ ክፍሎችን ምቹ በማድረግ ውጤታማ ስራዎች መሰራታቸውን ጠቁመዋል።

የጤና መድህን አገልግሎት ተደራሽነትን ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አንስተው÷ በዚህም 891 ሺህ ቤተሰብ የጤና መድህን አባል በመሆን 4 ነጥብ 5 ሚሊየን የክልሉን ሕዝብ ተጠቃሚ በማድረግ ከባለፈው ዓመት የተሻለ አፈጻጸም መመዝገቡን አመልክተዋል።

የእናቶችና ጨቅላ ህፃናት ሞት ለመቀነስ በርካታ የንቅናቄ ስራዎች በመስራት በዘርፉ ውጤት መመዝገቡንም መናገራቸውን የቢሮው ኮሙኒኬሽን ለፋና ዲጂታል ገልጿል።

በመንግስት የጤና ተቋማት የአገልግሎት አሰጣጥ፣ የግብዓት አቅርቦትና የሰው ኃይል እጥረትን ለሟሟላት ከአጋር አካላት ጋር በቅንጅት መሠራት እንዳለበት ገልጸው÷ የአገልግሎት ጥራት ላይ ትኩረት በማድረግ የታየውን ማስቀጠል ያስፈልጋል ብለዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.