Fana: At a Speed of Life!

አዲስ አበባ የአፍሪካ የማኅበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ጉባዔን ልታስተናግድ ነው

አዲስ አበባ፣ የካቲት 28፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የአፍሪካ የማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ጉባኤን ልታስተናግድ ነው።

ጉባኤውን በጋራ የሚያዘጋጁት ፐልስ ኦፍ አፍሪካ ሚዲያ እና ኤ.ጂ.ኤ ቴክ ኢንተርፕራይዝ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ÷ ጉባኤው በፈረንጆቹ ግንቦት 7 እና 8 ቀን 2026 በአዲስ አበባ የዓድዋ ድል መታሰቢያ እንደሚካሄድ ገልጸዋል።

ጉባኤው የአፍሪካን ተፅዕኖ ፈጣሪ ድምፆች ከመገናኛ ብዙኃን ድርጅቶች፣ ፖሊሲ አውጪዎችና የግሉ ዘርፍ መሪዎችን የሚያገናኝ ታሪካዊ የጋራ መድረክ መሆኑ ተገልጿል።

”ተፅዕኖ ለተሻለች አፍሪካ” በሚል መሪ ሐሳብ የሚካሄደው ጉባኤም የዲጂታል ተሳትፎ ፈጠራ፣ ቴክኖሎጂና ኃላፊነት ላይ ምክክር የሚደረግበት ወሳኝ መድረክ እንደሚሆን ይጠበቃል።

የፐልስ ኦፍ አፍሪካ አስተባባሪ በረከት ሲሳይ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ ጉባኤው ፈጣን ዕድገት እያስመዘገበ ባለው ሰው ሰራሽ አስተውሎት፣ የአፍሪካን የዲጂታል ገጽታና ይዘት ፈጠራ ላይ ትኩረት ያደርጋል።

በጉባኤ ምክክር ላይ የቴክኖሎጂ ሥነ-ምኅዳር ፈጠራ፣ የአፍሪካ ታሪክና መፃኢ ተስፋዎች ላይ ጥራት ያላቸው የይዘት ሥራዎችን ለማስተጋባት አቅም የሚፈጠር አሕጉራዊ መድረክ መሆኑን ገልጸዋል።

የአፍሪካ የማኅበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ጉባኤ ፕሮጀክት አስተባባሪ ባዩሽ ማሞ በበኩላቸው÷ ጉባኤው እያደገ በመጣው የዲጂታል ዓለም የአፍሪካን የዲጂታል ሥነ ምኅዳር ትብብርና ተወዳዳሪነት ለማጎልበት አቅም ይፈጥራል ብለዋል።

የአፍሪካ የማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ጉባኤ ይፋዊ ምዝገባ በቅርቡ እንደሚጀምር ገልጸው÷ የአሕጉሪቱን ዲጂታል መጻኢ የፈጠራ አቅምና እጣ ፋንታ በተሻለ ይዘት ለመቅረጽ ጉባኤው ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.