Fana: At a Speed of Life!

የገጠር ኮሪደር ልማት የአርሶ አደሩን የኑሮ ሁኔታ እያሻሻለ ነው – ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር) 

አዲስ አበባ፣ የካቲት 29፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የገጠር ኮሪደር ልማት ስራ የአርሶ አደሩን የኑሮ ሁኔታ እያሻሻለ ነው አሉ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር)፡፡

የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ከተጠሪ ተቋማቱ ጋር በመሆን በሲዳማ ክልል ዳራ ወረዳ በገጠር ኮሪደር ልማት ያስገነባቸውን አምስት መኖሪያ ቤቶችን በዛሬው ዕለት አስመርቋል።

በመርሐ ግብሩ ላይ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ፣ ሌሎች ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር) በወቅቱ እንዳሉት÷ ተቋሙ የተለያዩ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ስራዎችን በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች እያከናወነ ይገኛል።

በዛሬው ዕለት የተመረቁ የገጠር ኮሪደር ልማት መኖሪያ ቤቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ አካል መሆናቸው ተናግረዋል፡፡

የተገነቡት ቤቶች ዘመናዊና እና መሰረተ ልማቶች የተሟሉላቸው መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

ቤቶቹ የሌማት ቱሩፋት ስራዎችን፣ የጓሮ አትክልትና ፍራፍሬ፣ አማራጭ የሀይል እና ንፁህ የውሃ አቅርቦትን ጨምሮ ሌሎች መሠረታዊ ጉዳዮችን ያሟሉ መሆናቸውን አብራርተዋል።

የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ከተጠሪ ተቋማቱ በዚህ ረገድ የድርሻቸውን እየተወጡ እንደሆነ ገልጸው፤ መሰል ስራዎችን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

የአርሶ አደሩ ህይወት እንዲሻሻል መንግሥት በትኩረት እየሰራ መሆኑንም አመልክተዋል።

በጥላሁን ይልማ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.