የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጣናን መሰረት ያደረገ የጥራት ማረጋገጫ አገልግሎት እየተሰጠ ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ የካቲት 29፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጣናን እና የደረቅ ወደብን መሰረት ያደረገ የጥራት ማረጋገጫ አገልግሎት እየተሰጠ ነው አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ የትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፥ የኢትዮጵያ የተስማሚነት ምዘና ድርጅት የድሬዳዋ ቅርንጫፍ ጽ/ቤትን የሥራ እንቅስቃሴ ገልጸዋል፡፡
ድርጅቱ ዓለም አቀፍ የአሰራር ስርዓትን በመከተል ለአምራቾች፣ ለአገልግሎት ሰጪዎች፣ ለላኪዎች፣ ለአስመጪዎች፣ ለተቆጣጣሪ መስሪያ ቤቶች፣ ለምርምር ተቋማትና ለሸማቹ ማህበረሰብ የምርትና አገልግሎቶች የጥራት ማረጋገጫ አገልግሎትን እየሰጠ ነው ብለዋል፡፡
በድሬዳዋ አካባቢ ለሚገኙ አምራቾችና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ነፃ የንግድ ቀጣና እንዲሁም የደረቅ ወደብን መሰረት በማድረግ አዲስ የፍተሻ ላቦራቶሪ በማደራጀት አገልግሎቱን ተደራሽ አድርጓል ነው ያሉት።
ተቋሙ ከዚህ ቀደም በምግብ ዘይት፣ በነዳጅ ምርት፣ በተለያዩ የምግብ ምርቶች፣ ለማስዋቢያና የዲተርጀንት ምርቶች፣ ለኮንስትራክሽን ምርቶችና ግብዓቶች የጥራት ማረጋገጫ አገልግሎት በመስጠት ላይ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡