Fana: At a Speed of Life!

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በድሬዳዋ የእመርታ ቤተ መጻሕፍትን ጎበኙ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 30፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከመደመር መጻሕፍት ሽያጭ እና ከድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር በተገኘ በጀት የተገነባውን የእመርታ ቤተ መጻሕፍትን ጎብኝተዋል።

ቤተ መጻሕፍቱ ከ1 ሺህ ካሬ ሜትር በላይ የቦታ ስፋት ላይ ያረፈ እና ዘመናዊ መሠረተ ልማት እንዲኖረው ተደርጎ የተገነባ መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አስታውቋል።

ባለሦስት ወለል የሆነው እመርታ ቤተ መጻሕፍት ተጠቃሚዎች ተስማሚ የሆነውን የድሬዳዋን አየር እያገኙ እንዲገለገሉም የቴራስ ቦታ መዘጋጀቱ ተመላክቷል።

‎ቤተ መጻሕፍቱ የብሬል ማንበቢያ ቦታ፣ ለልዩ ፍላጎት ተጠቃሚዎች የተዘጋጀ የአይቲ ማዕከል፣ ከክፍል ውጭ የንባብ ቦታ፣ የግል እና የቡድን ማንበቢያና የጥናት ክፍሎች እንዲሁም የኮንፈረንስ ክፍል ያካተተ መሆኑን የጽሕፈት ቤቱ መረጃ አብራርቷል።

በአጠቃላይ እመርታ ቤተ መጻሕፍት በአንድ ጊዜ ለ1 ሺህ ሰው አገልግሎት መስጠት እንዲችል ሆኖ የተገነባ ሲሆን÷ በመጽሐፍ መደርመሪያው ላይ ብቻ 1 ሚሊየን መጻሕፍትን የመያዝ አቅም እንዳለውም ተገልጿል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.